ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጥረት ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን የሦስተኛ ሳምንት ቦሌ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ሜዳ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ ጥረት ኮርፖሬት ያገናኘው ጨዋታ 2 – 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

10:00 ላይ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጤቱ ነጥብ ተጋርተው ይውጡ እንጂ በኳስ ቁጥጥሩ ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫ በመውሰድ ከጥረት ኮርፖሬት የተሻሉ ነበሩ። ሴት ፈረሰኞቹ እንደወሰዱት ብልጫ ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸው አምስት ደቂቃ ሲሆን አጥቂዋ ዳግማዊት ወደ ጎል አክራ የመታችውን ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ስትተፋው መልካም ተፈራ ኳሱን አግኝታ ወደ ጎልነት በመቀየር ቅዱስ ጊዮርጊሶችን መሪ ማድረግ ችላለች። የመሀል ሜዳ ክፍሉ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ከተከላካዮቹ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ የግብ እድል ይፈጥሩ የነበሩት ጥረቶች ብዙ ሳይቆዩ በ8ኛው ደቂቃ በምስር ኢብራሂም አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል። 

በታዳጊ እና አዳዲስ ተጫዋቾች የተሞላው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስብ ከልምድ ማነስ የተነሳ በሚሰሩ ስህተቶች ጎል ለማስቆጠር የሚቸገር ቡድን ቢሆንም ጥረታቸው በድጋሚ ሰምሯል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት መልካም ተፈራ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና በሚገርም ብቃት አምክናው የተገኘውን የማዕዘን ምት ባልተገመተ ሁኔታ ከጥረት ተከላካዮች በቁመት አጠር የምትለው ዳግማዊት ሰለሞን በግንባሯ በመግጨት ግሩም ጎል አስቆጥራ ፈረሰኞች በ2-1 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ በ48ኛው ደቂቃ የጥረት አምበል ሩት ያደታ ከሳጥን ውጭ አክርራ የመታችውን የቅዱስ ጊዮርጊሷ ግብ ጠባቂ ከምባቴ ካታሌ ስትተፋው መዲና ጀማል አግኝታ ወደ ጎልነት በመቀየር ጥረቶችን አቻ ማድረግ ችላለች። ጥረቶች በፍጥነት ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው መመለሳቸው ተጨማሪ ጎሎች በቀሩት ደቂቃዎች እንደሚቆጠሩ ቢጠበቁም ከጠንካራ ፉክክር የዘለለ ለጎል የቀረበ ተጠቃሽ ሙከራ በሁለቱም ቡድኖች ሳንመለከት ጨዋታው  በ2 – 2 አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

በጨዋታ መጠቀስ ከሚገባቸው ነገሮች አንዱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አማካይዋ እሌኒ አበበ እና የግራ መስመር ተከላካይዋ ንግስት አስረስ በግላቸው የሚያደርጉት ጥረት እጅግ አስገራሚ የነበረ ሲሆን በስፍራው የነበረ ተመልካችም አድናቆቱን ለግሷቸዋል።