የአሰልጣኞች አስተያየት | ደቡብ ፖሊስ 0-1 ፋሲል ከነማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ዛሬ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ከፋሲል ከነማ ተገናኝተው አፄዎቹ 1-0 ካሸነፉበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡ 

“ሙሉ ጨዋታውን ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከተማ 

“ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን ገምተን ነበር። እንደሚታወቀው ተጋጣሚያችን ከሜዳው ውጭ ተሸንፈው ነው የመጡት። ተሸንፎ የመጣን ቡድን በሜዳው መግጠም ደግሞ በጣም ከባድ ነው። ቶሎ ቶሎ ለማጥቃት መከራን አድርገናል፤ ግን ብዙም የተሳካ አልነበረም። በተለይ ከእረፍት በፊት ለማጥቃት ሳጥን ውስጥ ስንደርስ ይቆራረጡ ነበር። ሆኖም ከሜዳ ውጭ እንደተደረገ ጨዋታ መጥፎ የምለው አይደለም። ሙሉ ደቂቃውንም ተጭነን ለመጫወት ሞክረናል። በነሱ በኩል አልፎ አልፎ የመልሶ ማጥቃቶች ነበሩ። በዛም ትንሽ ተቸግረን ነበር። ከዛ ውጭ ግን ጥሩ ነበርን።”

በጨዋታው ላይ ኤፍሬም ዓለሙን በተደጋጋሚ ሲጠሩት የነበረበት ምክንያት

“በተደጋጋሚ ከያስር ጋር ይደራረብ ነበር። ስለዚህ ጨዋታው ባላንስ መሆን አልቻለም። በአንድ መስመር ላይ ነበር የምናጠቃው። ሁለተኛ ደግሞ ከአጥቂው ጋር ያለው ግንኙነት በጣም የተራራቀ ነበር። ኳስ ሲደርሱትም መጠቀም ላይ ችግር ነበረበት። ከአማካይ ተነስቶ ከአጥቂዎች ጋር ተቀላቅሎ መጫወት ቢኖርበትም እዛ ቦታ ላይ አጣው ነበር። ይህንን ለማስተካከል ነበር የምናገረው፤ ወደ በኃላ ላይ ግን አሻሽሎታል። ሁለቱ አጥቂዎች ኢዙ እና ቤንጃሚንም ገና ናቸው። ከቡድኑ ኳስ ጋር ሲግባቡ ጥሩ ነገር ይፈጥራሉ ብዬ አስባለው።”

“ራሳችን በሰራነው ስህተት ግብ ተቆጥሮብናል” ያለው ተመስገን – የደቡብ ፖሊስ ረዳት አሰልጣኝ

ስለጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ በአብዛኛው የተሻለ እንቅስቃሴ ነበረው። ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ፈጥረን ነበር። ያገኘናቸውን ወደ ጎል መቀየር ባለመቻላችን እንደታየው በስተመጨረሻ እኛ ራሳችን በሰራነው ስህተት ጎል ሊቆጠርብን ችሏል። ይህንን ጎል የማግባት ችግራችንን ደግሞ በሚገባ ቀርፈን በቀጣይ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ጠንክረን የምንሰራ መሆኑን መናገር ችላለው።”

ወጥ የተጫዋቾች ምርጫ አለመኖር

“በርግጥ ዘግይተን ነው ሊጉን የተቀላቀልነው። አንዱ ተፅዕኖ እሱ ነው። በቡድኑ ወስጥ አንዳንድ የቅንጅት ችግሮች የሚመጡት አብረው ረጅም ጊዜ ባለመስራት ነው። ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ያለ ቡድን ነው። ውጤት አያምጣ እንጂ ጨዋታችን እያደገ ነው የመጣው። ስለዚህ አንዳንዴ ስህተት ይሰራሉ፤ እግር ኳስ ደግሞ ሁልጊዜም በስህተት የታጀበ ነው። እነዚህን በቀጣይ አርመን የተሻለ ነገር እንሰራለን። ያልተጠቀምናቸው ተጫዋቾችን በሒደት እየተጠቀምን ቋሚ ስብስብ በማውጣት የተሻለ ቡድን እንሰራለን፡፡ “