ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | የአምስተኛ ሳምንት 3ኛ ቀን ጨዋታዎች

ዛሬ እና ትናንት ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ነገ በአራት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። በሐረር ፣ ሀዋሳ ፣ ሽረ እና አዲስ አበባ የሚደረጉትን እነዚህን ጨዋታዎች በቅድመ ዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል። 

ድሬዳዋ ከተማ ከ ደደቢት

በመጀመሪያው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከተረቱ በኋላ ምንም ጨዋታ ያላደረጉት ድሬዳዋ ከተማዎች ነገ ደደቢትን ያስተናግዳሉ። ብርቱካናማዎች የስታድየማቸው ዕድሳት ባለመጠናቀቁ በሜዳቸው የሚያደርጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ ወደ ሐረር በማቅናት ነው የሚያከናውኑት። መጨረሻ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ደደቢት ወደ ሐረር የሚጓዘው ሦስት ጨዋታዎችን አድርጎ ያለምንም ነጥብ ሲሆን እስካሁን አምስት ግቦች ተቆጥረውበት አንድም ጊዜ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። በመሆኑም ጨዋታው በየትኛውም ውጤት ቢጠናቀቅ ሁለቱም ክለቦች አልያም አንዳቸው የመጀመሪያ የሊግ ነጥባቸውን የሚያሳኩበት አጋጣሚ የሚፈጠርበት ይሆናል። 

የድሬዳዋ ከተማዎቹ በረከት ሳሙኤል ፣ አማረ በቀለ እና ምንተስኖት የግሌ ጉዳት ላይ የሚገኙ በመሆኑ ይህ ጨዋታ የሚያመልጣቸው ሲሆን በደደቢት በኩል የተሰማ የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና ግን የለም።

ወጣቶች የተገነባው የደደቢት ቡድን እንደ እስካሁኑ ሁሉ ነገም ኳስ ተቆጣጥሮ ለመጫወት እንደሚሞክር ይጠበቃል። በዚሁ አጨዋወት በአለምአንተ ካሳ የሚመራው የቡድኑ የመሀል ክፍል በፍሬድ ሙሸንዲ ሽፋን የሚያገኘው የድሬዳዋን የኋላ ክፍል ሰብሮ በመግባት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቀላል ይሆንለታል ተብሎ አይጠበቅም። የአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ በቦታው መኖራቸው ሲታይ ደግሞ የመሀል ክፍሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለማግኘት ላይቸገር እንደሚችል ይጠቁማል። በመስመር አማካይነት የሚጠቀሟቸው የአጥቂ ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾቻቸውን ለጥቃት ዋነኛ መነሻ የሚያደርጉት ድሬዎች በተቃራኒው መሀል ሜዳ ላይ ኳስን ከማቆየት ይልቅ በሁለቱ መስመሮች ወደ ደደቢት የግብ ክልል ለመድረስ እንደሚጥሩ ይታሰባል። የፊት አጥቂዎቻቸው ጥምረትም ከመስመር አማካዮቹ በተጨማሪ በረጅሙ የሚላኩ ኳሶችን ወደ ግብነት የመቀየር ኃላፊነት ይኖርበታል። 

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ 12 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን 3 ጊዜ አቻ ሲለያዩ ደደቢት ሰባት ጊዜ ድሬደዋ ደግሞ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል። ከተቆጠሩት 23 ግቦችም ደደቢት የ16ቱ ድሬዳዋ ደግሞ የሰባቱ ባለቤቶች ናቸው።

– አምና በሁለቱም ዙሮች እርስ በእርስ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ። 

ዳኛ

– በ2009 ለስድስት ወራት ቅጣት ተላልፎበት የነበረው እና ያለፈውን አንድ ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ሲሰራ የቆየው ፌደራል ዳኛ ኄኖክ አክሊሉ ዳግም ወደ ሊጉ ተመልሶ ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሀንስ

ኃይሌ እሸቱ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ራምኬል ሎክ

ኢታሙና ኬይሙኒ – ሀብታሙ ወልዴ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

አብዱልአዚዝ ዳውድ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌክ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ 

አብርሀም ታምራት – ያብስራ ተስፋዬ

አቤል እንዳለ – አለምአንተ ካሳ – ያሬድ መሐመድ

አሌክሳንደር ዐወት

ሀዋሳ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

የሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ነገ ሦስተኛ የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታውን ያስተናግዳል። ሙሉ የሊግ ጨዋታቸውን ካደረጉ አራት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ሜዳው ላይ ያደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እንዲሁም ወደ ሰሜን ከተጓዘባቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በማሳካት 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የአምና ጥንካሬውን እያጣ የመጣው አዳማ በአንፃሩ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ድል ማግኘት ባይችልም ሁለት ነጥቦችን ይዞ ከነገ ተጋጣሚው በአስር ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ተቀምጧል። ነገር ግን ወትሮም ብርቱ ፉክክር የሚያስተናግደው እና ግብ የማያጣው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል። 

ሀዋሳ ከተማ ዮሀንስ ሴጌቦን በጉዳት ሲያጣ በድቻው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለተው አይቮሪኮስታዊው ተከላካይ ያኦ ኦሊቨር ስድስት ጨዋታ በመቀጣቱ ይህም ጨዋታ ያልፈዋል። ቅጣት የሌለባቸው አዳማዎች ደግሞ ዐመለ ሚልኪያስ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ ከንዓን ማርክነህ እና ሱራፌል ጌታቸውን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀሙ ይሆናል።

ጨዋታው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት በሚጥሩ ሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ እንደመሆኑ መጠን አጫጭር ቅብብሎች ሊበራከቱበት እንደሚችሉ ቢገመትም ከሜዳው ምቹነት አንፃር ፈጠን ያለ ሊሆን የምችልበት ዕድልም ይኖራል። በሀዋሳ በኩል እስከተጋጣሚ የግብ ክልል ድረስ ሲዘልቁ የሚታዩት የመስመር ተከላካዮች ወደ እስራኤል እሸቱ የሚልኳቸው ኳሶች ከነታፈሰ ሰለሞን ከሚነሱ ቅብብሎች በተጨማሪ ለእስራኤል ዕድሎችን እንደሚፈጥሩ ይታሰባል። የአማካይ ክፍላቸው ጥንካሬ በቀነሰው አዳማዎች በኩል የአምናውን ፈጣን የማጥቃት ሽግግራቸውን መልሰው ማግኘት ከቻሉ ከሀዋሳ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመገኘት የነዳዋ ሁቴሳ ፍጥነት ጥሩ ግብዓት ይሆናቸዋል። ከዛም በላይ ግን የኋላኛው የቡድኑ ክፍል የቀድሞው ጥንካሬውን ይዞ ካልቀረበ ነገ ሊቸገር የሚችልበት ዕድል ከፍ ማለቱ የማይቀር ነው።

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች አስካሁን 35 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ 16 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ በግማሽ አንሶ 8 ጊዜ ድል አድርጓል፡፡ በ11 አጋጣሚዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሀዋሳ 40 ጎሎች ሲያስቆጠር አዳማ ከተማ 35 አስቆጥሯል፡፡

– ሀዋሳ ላይ 17 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 8 ሲያሸንፍ አዳማ 3 ጊዜ አሸንፎ ተመልሷል፡፡ 8 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

– የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በርካታ ግቦች ከሚያስተናግዱ ግንኙነቶች መካከል ነው፡፡ በ1998 የውድድር ዘመን ሀዋሳ ላይ የተደረገው ጨዋታም ያለ ጎል የተጠናቀቀ ብቸኛ ግንኙነታቸው ነው።

–  አዳማ ከተማ ካለፉት 10 ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች በአንዱም ድል አስምግቦ አልተመለሰም፡፡ (በሲዳማ ቡና የተሸነፈበት ጨዋታ ከቀናት በኋላ ፎርፌ መሰጠቱን ልብ ይሏል)

ዳኛ

– በመጀመሪያው ሳምንት ሀዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ.ዩ በመዳኘት አምስት የቢጫ ካርዶች የመዘዘው ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል፡፡

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-3-3) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

አዲስዓለም ተስፋዬ – መሣይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

ታፈሰ ሰለሞን – ምንተስኖት አበራ – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን

አክሊሉ ተፈራ – እስራኤል እሸቱ – ኄኖክ ድልቢ

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አንዳርጋቸው ይላቅ – ምኞት ደበበ – ቴዎድሮስ በቀለ –  ሱለይማን መሐመድ 

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሆቴሳ – ሙሉቀን ታሪኩ – ቡልቻ ሹራ

ስሑል ሽረ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ እና የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጎላቸውን ለማግኘት በመጠበቅ ላይ የሚገኙት አዲስ አዳጊዎቹ ስሑል ሽረዎች የሊጉ ሻምፒዮኖችን ያስተናግዳሉ። ሽረዎች ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው ከባድ ሽንፈት ባለፈ በሜዳቸው ካደረጓቸው የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎችም ሙሉ ነጥብ ማሳካት አልቻሉም። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ጨዋታ ድል በማድረግ ወደ ሊጉ የተመለሱት አባ ጅፋሮች አዳማን ከረቱበት የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ሁለተኛ የሜዳ ውጪ ጨዋታቸውን ወደ ሽረ ተጉዘው የሚያደርጉ ይሆናል። ቻምፒዮኖቹ በፕሪምየር ሊጉ የአስራ ስድስት ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዟቸውንም ላለማስደፈር ጭምር ወደ ሜዳ የሚገቡበት ጨዋታ ነው። 

የስሑል ሽረዎቹ ኄኖክ ካሳሁን ፣ ሸዊት ዮሀንስ ፣ መብራቱ ክፍሎም እና ሠለሞን ገብረመድህን ጉዳት ላይ በመሆናቸው ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በጅማ በኩል ደግሞ ዘሪሁን ታደለ ጉዳት ላይ የሚገኝ ብቸኛው ተጫዋች ነው። በሌላ በኩል በቻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ ላይ በጉዳት ያልነበሩት የአባ ጅፋሮቹ ቢስማርክ አፒያ እና ዐወት ገብረሚካኤል ለነገው ጨዋታ ይደርሳሉ።

ባለሜዳዎቹ ስሑል ሽረዎች በርካታ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉባቸው የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ አሳይቷቸዋል። በተለይም በአጥቂ እና አማካይ ክፍሉ መካከል ያለውን ግንኙነት ካላሻሻለ በአባጅፋር የመሀል ክፍል የመዋጥ አደጋ እና የግብ ዕድሎችንም ለመፍጠር የሚቸገሩበት ሁኔታ መፈጠሩ የሚቀር አይመስልም። የመስመር ጥቃቶችን ለማክሸፍም የተከላካይ መስመሩ የሜዳውን ስፋት በአግባቡ የማይሸፍን ከሆን ለአስቻለው ግርማ እና ዲዲዬ ለብሪ የመስመር ጥቃት በእጅጉ ይጋለጣል። ሁለቱ የአባ ጅፋር አጥቂዎች ከማማዱ ሲዲቤ ጋር በመሆን የባለሜዳዎቹን የኋላ ክፍል በፈጣን የማጥቃት ሽግግር እንደሚፈትኑም ማሰብ ይቻላ። ሻምፒዮኖቹ ከዚህ በተጨማሪ ዘግይተው ወደ ሳጥን የሚገቡ የአማካይ መስመር ተጫዋቾቻቸውም ተጨማሪ ጥንካሬ እንደሚያላብሷቸው ይገመታል። 

ዳኛ

 – ጨዋታውን በሦስተኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በአራተኛ ዳኝነት ተመድቦ የነበረው ተከተል ተሾመ ይመራዋል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

ሙሉጌታ ዓንዶም – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ደሳለኝ ደባሽ – አሸናፊ እንዳለ 

ኢብራሂማ ፎፋና – ጅላሎ ሻፊ – ኪዳኔ አሰፋ               

ሚድ ፎፋና

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጃዬ

ዐወት ገብረሚካኤል – ተስፋዬ መላኩ – አዳማ ሲሶኮ – ኤልያስ አታሮ

ይሁን እንዳሻው – ኄኖክ ገምቴሳ – ኤልያስ ማሞ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ከአምስተኛው ሳምንት መርሀ ግብር ውስጥ ነገ በብቸኝነት አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው ጨዋታ በ10፡00 ኢትዮጵያ ቡናን ከወላይታ ድቻ ያገናኛል። ድሬዳዋን በመርታት ሊጉን የጀመሩት ቡናዎች ከቀጣዮቹ ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ካሳኩ በኋላ ነው ወደ መዲናዋ የሚመለሱት። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያልተቆጠረባቸው ቡናማዎቹ በሰባት ነጥቦች ሊጉን በመምራት ላይም ይገኛሉ። ቀዝቀዝ ብለው ሊጉን በመጀመር በሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያሳኩት ድቻዎች በበኩላቸው ሳምንት መቐለን በመርታት ወደ ሊጉ ወገብ ከፍ ብለው ለነገው ጨዋታ ደርሰዋል። 

ኢትዮጵያ ቡና አህመድ ረሺድ ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን እና አስራት ቱንጆን በጉዳት የማያሰልፍ ሲሆን የወላይታ ድቻዎቹ ባዬ ገዛኸኝ ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ ኃይማኖት ወርቁ ፣ እርቂሁን ተስፋዬ እና አምበሉን ተክሉ ታፈሰ በተመሳሳይ ጉዳት ላይ ይገኛሉ። ድቻዎች በአንፃሩ ውብሸት ክፍሌን ከጉዳት መልስ የሚያገኙ ይሆናል።

የአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ቡድን ኳስን ለመቆጣጠር ከሚያሳየው ፍላጎት በተጨማሪ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክር እና ኳስን ሲነጠቅ በቶሎ መልሶ ለማግኘት ሲጥር ይታያል። ይህ ባህሪውም ነገ በአመዛኙ ወጣት የሆኑ አምስት አማካዮችን ከሚጠቀመው ወላይታ ድቻ ጋር ሲገናኝ የሚኖረውን የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። የወላይታ ድቻ የመስመር አማካዮች ጫና ውስጥ ገብተው ከማጥቃት ዞኑ ርቀው  ብቸኛውን ተከላካይ አማካያቸውን በመርዳት ካልተጠመዱ በቀርም ለቡድናቸው ዋነኛ የማጥቃት መሳሪያ እንደሚሆኑ ይገመታል። በኢትዮጵያ ቡናም በኩል ከኋላ ተመስርቶ የሚመጣው አብዛኛው ኳስ በመስመር አጥቂዎቹ በኩል ወደ ድቻ ሳጥን እንዲደርስ የሚደረግ ከሆነ ጨዋታው በመስመር እንቅስቃሴዎች የሚወሰንበት ዕድል ከፍ ያለ ነው። 

የእርስ በስርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአስር ጊዜያት ሲገናኙ  ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ጊዜ ወላይታ ድቻ ደግሞ ሁለት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በቀሪዎቹ 5 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተለያዩ ሲሆን ቡና ስምንት ድቻ ደግሞ ሰባት  ግቦችን አስቆጥረዋል።                                         

– አዲስ አበባ ላይ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና 2 ጊዜ ሲያሸንፍ 3 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። 
ዳኛ

– ይህን ጨዋታ ከከፍተኛ ሊግ ካደጉ ዳኞች መካከል አንዱ የሆነው ዮናስ ገረመው በዋና ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ዋቴንጋ ኢስማ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታንቢ – ተካልኝ ደጀኔ

ሳምሶን ጥላሁን  – ዳንኤል ደምሴ – ካሉሻ አልሀሰን

አቡበከር ነስሩ – ሎክዋ ሱሌይማን – ሚኪያስ መኮንን

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ሙባረክ ሽኩር – ኄኖክ አርፊጮ

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ኄኖክ ኢሳያስ – እዮብ ዓለማየሁ

አንዱዓለም ንጉሴ