የአሰልጣኞች አስተያየት| ሀዋሳ ከተማ 2-0 አዳማ ከተማ

ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን አስተናግዶ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ከረታበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱም ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየቶቻቸውን እንደሚከተለው ሰጥተውናል ፡፡

“የበለጠ የተሻለ ለመሆን እንሞክራለን” አዲሴ ካሳ (ሀዋሳ ከተማ)

ስለጨዋታው…

” ጥሩ ነው ፤ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደረግን ያለነው መሻሻል። አሁንም ግን ይቀረናል። በተለይ ጎል የማግባት እና የመጨረሻው የመጫወቻ ቦታ ላይ ትንሽ የመጓጓት እና የመቻኮል ነገሮች አሉ። በተረፈ በሜዳችን ያለን ነገር ጥሩ ነው። በተለይ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ እየደረስንም ስለሆነ ይህ ችግርም ሊቀረፍ የሚችል ነው። በሚቀጥለው እነዚህን አስተካክለን የበለጠ የተሻለ ለመሆን እንሞክራለን። ”

የአጨራረስ ችግሩ የሚኖረው ተፅዕኖ

” በይበልጥ እየሰራን ያለነው እዚህ ላይ ነው። መታየትም ያለበት ተጫዋቾቼ ልምድ የላቸውም። ማጥቃት ላይ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው በየጊዜው በምንሰራው ልምምድ ነው። ትልቁ ነገር ግን የተጋጣሚ ቡድን ጋር ወደ ግብ መድረስ ነው። አሁን እየደረስን ነው። ከባህር ዳር ጋር አቻ ስንወጣ ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር። የታየብን ችግርም ይህ ነገር ነው። ይሄም ሊሆን የቻለው ከፍተኛ ልምድ ያለው አጥቂ ስለሌለን ነው። አሁንም እምነታችን በነዚህ ወጣት ልጆች ላይ ቶሎ ቶሎ እየሰሩ እንዴት ማግባት እንዳለባቸው ልምምድ ላይ ማስኬድ ነው። ይህን የፈጠረውም የልምድ ጉዳይ እና የማሸነፍ ጉጉታችን ይመስለኛል። ቡድኑ ጎል ያላገባው የባህር ዳሩ ጨዋታ ላይ ብቻ ነው። ሌላ በአራቱም ጨዋታችን ላይ አግብተናል። የአጨራረስ ችግራችን ጎልቶ ሊታይ የቻለው ደግሞ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረሳችን ይመስለኛል። ”


“ደጋፊው የሚፈልገውን ስላላገኘ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” ሲሳይ አብርሃም (አዳማ ከተማ)

ስለውጤት ማጣት…

” ኳስ ነው ፤ ለማስተካከል እየጣርን ነው። ስህተቶች ይኖራሉ። ዛሬ ካየን ተከላካዩ ማውጣት እየቻለ አላገኘውም ፤ ሳተው ከዛም ተቆጠረ። እኛም ያገኘነውን አልተጠቀምንም። ያ ነው ችግር የፈጠረብን። ይህ ኳስ ነው ፤ ለማስተካከል እየሞከርን ነው። ግን እንደስራችን ማግኘት ያለብንን አላገኘንም። ያለማሸነፋችን ችግር ካለመረጋጋት እና ከአዕምሯዊ ችግርች የመጣ ነው። ይህን ደግሞ ሙያተኛ ቀጥረን እንሰራበታል። ተጫዋቾቼ የአቅም ችግር የለባቸውም። በግል በሚደረጉ ስህተቶች ነው ግብ እየተቆጠሩብን ያሉት። በኳስ ደግሞ ስህተት ይኖራል ለማስተካከል ደግሞ ይሰራል። እንደ አሰልጣኝ ሁሌ ወደ ፊት ጥሩ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለው። ደጋፊውም ሊረጋጋ ይገባል። የሚፈለገውን ነገር ስላላገኘም ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው። ደጋፊው የሚለውን እንቀበላለን ለማስተካከልም እንጥራለን።

በጨዋታው ፍፃሜ ደጋፊዎች ያሰሙት ተቃውሞ …

” ደጋፊውን ለመካስ ጠንክረን እንሰራለን። ገና ነው ውድድሩ ፤ ገና አራተኛ ጨዋታ ነው ። ቀሪ 26 ጨዋታዎች ይቀራሉ። ደጋፊው እውነት አለው ፤ ቢናገር አይገርም። ነገር ግን ሊታገስ ይገባል። ብዙ ወጣት ተጫዋች ነው የያዝነው። ከከፍተኛ ሊግ የመጡ ናቸው። የተጫዋች ገበያውንም ባለቀ ሰዓት ነው የተቀላቀልነው። ባሉት ልጆች የተሻለ ነገር ለመስራት ትንሽ ጊዜ ይፈልጋል። ታች የነበሩ ልጆች ናቸው እነሱ ላይ ሰርተን ለማሸነፍ እንሞክራለን። በቀጣይ ማሸነፍ እንችላለን ፤ ስታሸንፍ ደግሞ በአንዴ ላይ ነው ምትወጣው። በርካታ ተጫዋቾች ደግሞ ተጎድተዋል። ከንዓን ፣ ዐመለ ፣ ቡልቻ እና ሌሎች ተጫዋቾች የሉም። ይህ እግር ኳስ ነው። ፍፁም ቡድንም የለም። ደጋፊው ረጅም ርቀት መጥቶ ውጤት በማጣቱ ወደ ፊት ሰርተን እንክሰዋለን። ተጋግዘን መስራት እንጂ መሳደብ ጥሩ አይደለም። በተጫዋቾቼ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ይህ ሚቀጥል ከሆነ ጥሩ ነገር አይኖርም። “