ከፍተኛ ሊግ ሀ | ወልዲያ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች ተካሂደው ወልዲያ እና ለገጣፎ በሜዳቸው፤ ደሴ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል። ኤሌክትሪክ እና ሰበታ ከተማ ደግሞ ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። 

በ10:00 ሰዓት ላይ በኦሜድላ ሜዳ ፌደራል ፖሊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ ምንም ጎል ሳይስተናገድበት ተጠናቋል። አስራ አምስት ደቂቃዎች ዘግይቶ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ውስጥ በእንቅስቃሴ ሆነ በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተክሉ ተስፋዬ እንዲሁም በኄኖክ መሀሪ አማካይነት የግብ ሙከራ አድርገዋል። ቀስ በቀስ ወደ እንቅስቃሴ የገቡት ፌደራል ፖሊሶች ወደፊት ኳስን በረጅሙ በማሻገር የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ስህተትን ሲፈትሹ ታይተዋል። በ29ኛው ደቂቃ በዚሁ አጋጣሚ የተገኘችውን የግብ እድል እንዳለማው ታደሠ አግኝቶ ሳይጠቀምባት ሲቀር በ42ኛው ደቂቃ ታዬ አስማረ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ በአጥቂ መስመሩ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰይፉ ዝክር ሞክሮ በግቡ የቀኝ አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። በ34ኛው ደቂቃ ከአቤል አክሊሉ የተሻገረርትን ኳስ ተክሉ ከግብ ጠባቂው ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረውም ተጠቃሸ የኤሌክትሪክ ሙከራ ነበር። 


ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አንጋፋው ታፈሰ ተስፋዬ በ50ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ሲያደርግ በ65ኛው ደቂቃ ላይ የፌዴራል ፖሊሱ በፍቃዱ ዓለማየሁ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ወንድወሰን ገረመው አድኖበታል። በ70ኛው ደቂቃ ላይም አዳነ ተካ ተመሳሳይ ኳስ አግኝቶ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

የጨዋታው ጌዜ በገፋ ቁጥር መከላከል ላይ የተጠመዱት ፌዴራሎች በረጅሙ ኳስ ወደ ፊት በመጣል ላይ ሲያተኩሩ ኤሌክትሪኮች ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ አጋጣሚዎችን አምክነዋል። በ72ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ ከሄኖክ መሀሪ ያገኘውን አጋጣሚ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ሲተፋው አቤል አክሊሉ አግኝቶ ቢሞክረውም የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣችበትም በአስቆጭነቱ የሚጠቀስ ነው። ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ4 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ወልዲያ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም ላይ ገላን ከተማን ያስተናገደው ወልዲያ 3-0 በማሸነፍ ምድቡን መምራት ጀምሯል። በክረምቱ ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው ተስፋዬ ነጋሽ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ኢድሪስ ሰዒድ ቀሪዋን የድል ጎል አስቆጥሯል። 

ከሜዳው ውጪ የተጫወቱት ደሴ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ድል አስመዝግበዋል። ወደ ባህርዳር ያቀናው ደሴ ከተማ አውስኮድን 2-0 ሲረታ አትክልት ንጉሴ ሁለቱንም የድል ጎሎች አስቆጥሯል። አቃቂ ቃሊቲ ደግሞ ወደ ኮምቦልቻ አምርቶ ወሎ ኮምቦልቻን በ70ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ተሾመ ባስቆጠረው ጎል 1-0 አሸንፏል።

ለገጣፎ ላይ ቡራዩ ከተማን ያስተናገደው ለገጣፎ ለገዳዲ ሳዲቅ ተማም በ86ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 ሲያሸንፍ አክሱም ከተማ ከሰበታ ከተማ 1-1 ተጠናቋል።