ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የሰርካዲስ ጉታ ጎሎች ለአዳማ ሦስት ነጥቦች አስገኝተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር አንደኛ ዲቪዝዮን የቀን ለውጥ የተደረገበትና የሶስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከአዳማ ከተማ አገናኝቶ አዳማ ከተማ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ሰርካዲስ ጉታ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች ታግዞ ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቷል፡፡

አዳማ ከተማዎች ፍፁም የበላይ በነበሩበት የመጀመሪያ 15 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሜዳ አጋማሽ አድልቶ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አዳማዎች ከመሀል ሜዳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በዘለለ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይም በጨዋታ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለችው የመስመር አጥቂ ሰርካዲስ ጉታ በ8ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ያገኘችውና ወደ ግብ ልካት የግቡ ቋሚ የመለሰባትና እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሰርካዲስ በድጋሚ አግኝታ ወደ ግብ የላከቻትና የአዲስ አበባዋ ግብጠባቂ እንደምንም ያዳነችባት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት እንግዶቹ አዳማ ከተማዎች በ23ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ከሁለት የአዲስአበባ ተጫዋቾች ጋር ታግላ ያቀበለቻትን ኳስ ሰናይት ቦጋለ ከአዲስ አበባዎች የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ወደ ግብ ብትልክም ኳሷ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወጥታለች። እጅግ ተዳክመው የቀረቡት አዲስአበባ ከተማዎች የጨዋታውን የመጀመሪያና በመጀመሪያ አጋማሽ ያደረጉትን ብቸኛ ሙከራ ለማድረግ 35 ያክል ደቂቃዎች አስፈልገዋቸዋል ፤ በዚህም አስካለ ከመስመር ያሻማችውን የቅጣት ምት በአዳማ ተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረችው ህይወት ረጉ በቀጥታ ወደ ግብ የላከቻት ኳስ በአዳማዋ ግብ ጠባቂ አድናባታለች፡፡

በመጀመሪያ አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት አዳማዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ገነት ኃይሉ ከመስመር ያሻገረችውን ኳስ ተጠቅማ ሰርካዲስ ጉታ በጥሩ አጨራረስ ቡድኗን ቀዳሚ ማረግ ችላለች፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ሴናፍ ዋቁማ ከመስመር ያሻገረለችላትን ኳስ ተጠቅማ የጨዋታው ኮከቧ ሰርካዲስ ጉታ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ያሳደጉበትን ግብ ማስቆጠር ችላለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አማካይዋ ቅድስት ቦጋለን ቀይረው ወደ ሜዳ ያስገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን መውሰድ ችለዋል፡፡ ገና በ46ኛው ደቂቃ በፎዚያ መሀመድ ጥሩ ሙከራን ማድረግም ችለዋል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ሁለተኛ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ መድረስ ባይችሉም ጥሩ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በዚሁ አጋማሽ ከተፈጠሩት ጥቂት የግብ ሙከራዎች መካከል በ80ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ ከአዲስአበባዋ ግብጠባቂ ሳሳሁልሽ ሥዩም ጋር ተገናኝታ ያመከነችበት ኳስ በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የአዳማ ከተማዋ ተከላካይ ወይንሸት ፀጋዬ ባጋጠማት ከባድ ጉዳት ከሜዳ ተቀይራ ለመውጣት ተገዳለች፡፡


4ኛ ሳምንት
ቅዳሜ ታኅሳስ 6 ቀን 2011
መከላከያ 08:00 አርባምንጭ ከተማ
ጥረት ኮርፖሬት 09:00 ጌዴኦ ዲላ
አዳማ ከተማ 09:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮ ንግድ ባንክ 10:00 ድሬዳዋ ከተማ
እሁድ ታኅሳስ 7 ቀን 2011
ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 09:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዋሳ ከተማ 09:00 አዲስ አበባ ከተማ