​በፕሪምየር ሊጉ ስድስተኛ ሳምንት አንድ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ እንደሚካሄዱ ሲጠበቅ አንድ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ መራዘሙን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። 

ጅማ አባ ጅፋር ከ ደደቢት እሁድ ጅማ ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በጅማ አባ ጅፋር የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል። ክለቡ ነገ ሌሊት ወደ ካይሮ የሚጓዝ ሲሆን ዓርብ ከግብፁ ኃያል አል አህሊ ጋር በአንደኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታውን ያደርጋል። 

ጅማ አባ ጅፋር በፕሪምየር ሊጉ ማድረግ ከነበረበት አምስት መርሐ ግብር ሁለቱን ብቻ ያከናወነ ሲሆን በስድሰተኛ ሳምንት ከደደቢት የሚያደርገው ጨዋታ ከመሸጋገሩ በተጨማሪ በ7ኛ ሳምንት ከሲዳማ ቡና የሚያደርገው ጨዋታም በቻምፒየንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ ምክንያት የመከናወኑ ነገር አጠራጣሪ ነው። 

በፕሪምየር ሊጉ የአምስት ሳምንታት ጉዞ ብቻ እስካሁን 12 ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፈዋል።