ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን | አቃቂ ቃሊቲ ሲያሸንፍ ልደታ እና ቦሌ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነው አቃቂ ቃሊቲ ድል ሲያስመዘግብ ልደታ እና ቦሌ አቻ ተለያይተዋል።

ሁለት ቡድኖች ራሳቸውን ከሊጉ በማግለላቸው ምክንያት በቅድሚያ የወጣው መርሐ ግብር በመፋለሱ በድጋሚ በወጣው ፕሮግራም መሠረት የሶስተኛ ሳምንት በዚህ ሳምንት ተካዷል። እሁድ ወደ ሻሸመኔ ያመራው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ባለሜዳው ሻሸመኔ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ወደ መሪነት ሲሸጋገር ሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዷል።

09:00 ላይ ልደታ ክፍለ ከተማን ከ ቦሌ ክፍለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት ልደታዎች በነጻነት ደርቤ የ17ኛ ደቂቃ ጎል ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችሉም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ቦሌዎች የጨዋታው የመጨረሻው የኳስ ንክኪ የሆነው የማዕዘን ምት ሲሻማ በልደታ ተከላካይ ተገጭቶ በራስ ግብ ላይ በተቆጠረ ጎል አቻ ሆነው ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

11:00 ላይ ንፋስ ስልክን የገጠመው አቃቂ ቃሊቲ በ58ኛው ደቂቃ ሠላማዊት ኃይሌ ባስቆጠረችው ጎል 1-0 አሸንፏል። በጨዋታው የበላይ የነበሩት አቃቂዎች በተለይ ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች በርካታ የግብ አጋጣሚዎች የፈጠሩ ሲሆን በተለይ ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ዙፋን ደፈርሳ በሁለት አጋጣሚዎች ከቅጣት ምት በቀጥታ የሞከረቻቸው ኳሶች አግዳሚውን ገጭተው ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በዚህ ሳምንት መቐለ ላይ ሊደረግ የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


4ኛ ሳምንት
ማክሰኞ ታኅሳስ 9 ቀን 2011
መቐለ 70 እንደርታ 09:00 ቂርቆስ ክ/ከተማ
ልደታ ክ/ከተማ 09:00 ፋሲል ከነማ
ሻሸመኔ ከተማ 09:00 አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ
ንፋስ ስልክ ላፍቶ 11:00 ቦሌ ክ/ከተማ