የትግራይ እና አማራ ክልል ክለቦች ከስምምነት ደርሰዋል

የትግራይ እና አማራ ክልል ክለቦች ዛሬ ባደረጉት ስብሰባ የእርስ በርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው ለማድረግ ተስማምተዋል። 

ዛሬ በጁፒተር ሆቴል ለሚድያዎች ዝግ በነበረው ስብሰባ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር መኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የሁለቱ ክልሎች ክለብ ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በመሩት ስብሰባ ሁለቱም ወገኖች የእርስ በእርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

በዚህም መሠረት ባለፉት አምስት ሳምንታት ሊደረጉ የነበሩና ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግረው የነበሩት የባህር ዳር ከተማ እና ስሑል ሽረ፣ የፋሲል ከነማ እና መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም የመቐለ 70 እንደርታ እና ባህር ዳር ከተማዎች በባለሜዳዎቹ ከተማ እንዲካሄድ ተስማምተዋል።

በሀገሪቱ በቅርብ ጊዜያት የተከሰተውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ተከትሎ በሁለቱ ክልሎች ክለቦች መካከል ከኅዳር 9 ቀን 2010 ወዲህ በየሜዳቸው የእርስ በርስ ጨዋታ ተከናውኖ አያውቅም።