ቻምፒዮንስ ሊግ | ወቅታዊ መረጃዎች በጅማ አባ ጅፋር ጉዞ ዙሪያ

ጅማ አባ ጅፋር የምሽቱን ጨዋታ ወደሚያደርግበት ከተማ ደርሷል።

ወደ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ድልድል ለማምራት ከግብፁ አል አህሊ ጋር ምሽት 02፡00 ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን እንደሚያደርግ የሚጠበቀው የጅማ አባ ጅፋር ልዑካን ቡድን አሌክሳንድሪያ በመግባት ዕረፍት እያደረገ ይገኛል።

ዕኩለ ለሊት ላይ ከአዲስ አበባ የተነሳው ቡድኑ ከሦስት ሰዓት በረራ በኋላ ነበር በግብጿ ካይሮ ከተማ የደረሰው። በመቀጠልም የሁለት ሰዓት ከሠላሳ የመኪና ጉዞ በማድረግ ንጋት 01፡30 አካባቢ ጨዋታው የሚደረግበት ቦርግ አላ አርብ ስታድየም መገኛ ወደ ሆነችው አሌክሳንድሪያ መድረስ ችሏል። ለስታድየሙ ቅርብ በሆነው ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ማረፊያቸውን ያደረጉት ጅማዎች ቀጣዮቹን ሰዓታት ዕረፍት ለማድረግ የተጠቀሙባቸው ሲሆን አሁን ላይ ምሳ ተመግበው ጨርሰዋል ፤ በመቀጠልም ወደ ቡድን ውይይት እንደሚያመሩ ይጠበቃል። አካባቢው ለሜዲትራንያን ባህር ቅርብ በመሆኑ ቀዝቃዛማ አየር አንዳለም ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ከሰዓታት በኋላ የሁለቱን ቡድኖች የመጀመሪያ አሰላለፍ እና ጨዋታውን የመከታተያ አማራጮች ይዘን እንመለሳለን።