ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ወደ አስመራ ያመራሉ

ነገ ኤርትራ ላይ የሚደረግ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ በሦስት ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ይመራል።

እንደ ሀገር ዳግም ወዳጅነታቸውን የጀመሩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በእግር ኳሱም መድረክ የሚያገናኛቸው አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይኸው አጋጣሚ እርስ በእርስ በሚደረግ ጨዋታ የተፈጠረ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ዳኞች በሚመሩት የወዳጅነት ጨዋታ የተገኘ ነው። ጨዋታው የኤርትራ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር ነገ በ10 ሰዓት በአስመራ የሚያደርገው ሲሆን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በእግር ኳሱ ባላቸው ግንኙነት አዲስ ምዕራፍን እንደሚከፍትም ታምኖበታል።

የኤርትራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ዳኞች እንዲመደቡለት በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ነው ዳኞቹ የወዳጅነቱን ጨዋታ ለመምራት ወደ ስፍራው ያመሩት። በዚህም መሰረት ብሩክ የማነብርሀን በዋና ዳኝነት ፣ ክንዴ ሙሴ እና ክንፈ ይልማ ደግሞ በረዳት ዳኝነት የነገውን የወዳጅነት ጨዋታ ይዳኛሉ። በቅርቡ ሁለቱ ሀገራት ወደ ሰላም ከመጡ በኃላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨምሮ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ከኤርትራ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ያሰቡ ቢሆንም ሳይሳካ የቀረ ሲሆን በሦስቱ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች የእግር ኳስ ግንኙነቱ የሚጀመር ይሆናል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቶታል ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ጅቡቲ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ከጅቡቲው ቴሌኮም ጋር ያደረገውን የመጀመርያ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ኤርትራዉያን ዳኞች መዳኘታቸው ይታወሳል፡፡