ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ

ከስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በመጨረሻ የሚደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታን የተመለከተው ዳሰሳችንን እንሆ።

በ2010 የውድድር ዓመት በጭቃማው የመጨረሻ ሳምንት ተገናኝተው የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ሠላሳ ዘጠነኛ የሊግ ጨዋታቸውን ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ ያደርጋሉ። ሀዋሳ ላይ በሲዳማ ቡና ተረተው የሊግ አጀማመራቸውን በሁለት ተከታታይ ድል የማስተካከል አጋጣሚያቸውን ያበላሹት ፈረሰኞቹ ከሁለተኛው የሜዳ ጨዋታቸው ነጥብ የማግኘት ግዴታ ውስጥ የገቡ ይመስላሉ። በዝውውር መስኮቱ እምብዛም ሳይሳተፉ በክለቡ ባደጉ ወጣቶች ላይ ተመስርተው ዓመቱን የጀመሩት ሀዋሳዎች ግን ከተጋጣሚያቸው በተሻለ አጀማመር ሊጉን እየመሩ ነው ወደ መዲናዋ የመጡት። ከአምስት ጨዋታዎች አስር ነጥቦችን የሰበሰቡት ሀዋሳዎች በርካታ ግቦችንም በማስቆጠርም በሊጉ ካሉ ክለቦች የተሻሉ ናቸው። በነገው ጨዋታም ሀዋሳዎች መሪነታቸውን ጠብቀው ለመቀጠል ቅዱስ ጊዮርጊሶችም አካሄዳቸውን ለማስተካከል ይገናኛሉ። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከረጅም ጊዜ በኃላ አጥቂው  ሳላህዲን ሰይድን ከጉዳት መልስ ነገ በተጠባባቂ ወንበር ላይ  በማስቀመጥ ሲጀምር በሲዳማው ጨዋታ መጨረሻ የልምምድ ወቅት በመጠነኛ ጉዳት ያልተሰለፈው ሳላህዲን ባርጊቾ ወደ ሜዳ ይመለሳል። መሀሪ መና ፣ አሜ መሀመድ ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሣምንት በጉዳት ተቀይሮ የወጣው አምበሉ ምንተስኖት አዳነ ግን በጉዳት ለነገ የማይደርሱ ይሆናል፡፡ በሀዋሳ ከተማ በኩል ረዘም ያለ ጉዳት የገጠመው ዮሃንስ ሴጌቦ የማይኖር ሲሆን ቅጣት ላይ የሚገኙት አዳነ ግርማ እና አይቮሪኮስታዊው ተከላካይ ያኦ ኦሊቨርም ጨዋታው ያልፋቸዋል። በመሆኑም ላለፉት አስር ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያሳለፈው አዳነ ግርማ የቀድሞው ክለቡን ሊገጥም ይችልበት የነበረው የታሪክ አጋጣሚ በቅጣት ያመልጠዋል።

ጨዋታው በአጨዋወት ረገድ ለውጥ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን የሚያገናኝ እንደመሆኑ ለውጦቹ እንደሚንፀባረቁበት ይጠበቃል። በሦስት የኋላ ተከላካዮች መጠቀም የጀመረው የስትዋርት ሀሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈጣኖቹን የመስመር ተመላላሾች አብዱልከሪም መሀመድ እና ኄኖክ አዱኛን ዋነኛ የጥቃት መሳሪያዎቹ አድርጎ ይጠቀማል። በተመሳሳይ ከአጫጭር ቅብብሎች ይልቅ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ መጠቀሙ ያደላው ሀዋሳ ከተማ የመስመር ተከላካዮቹ ተሻጋሪ ኳሶች ለብቸኛው አጥቂ የግብ ዕድል የሚፈጥርባቸው መንገዶቹ ናቸው። በመሆኑም ጨዋታው በሁለቱ ኮሪደሮች  በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የመወሰን ዕድሉ የሰፋ ነው። ከዚህ ውጪ ሀዋሳ በታፈሰ ሰለሞን መሪነት የሚሰነዝረው የመሀል ለመሀል ጥቃትም ሆነ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል የሚተገበር ተመሳሳይ አካሄድ ቡድኖቹ በሚጠቀሟቸው ሁለት ሁለት የተከላካይ አማካዮች ጥብቅ መከላከል እንደሚገጥመው ይታሰባል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት እውነታዎች

– ክለቦቹ በሊጉ 38 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 24 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ 7 ጊዜ ድል ሲቀናቸው ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 

– በ38ቱ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 67 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 31 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት በድምሩ 98 ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ነገ የግቦቹ መጠን 100 እንደሚደፍን ይጠበቃል። 

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለሥላሴ ይህን ጨዋታ ለመዳኘት ተመርጧል። አርቢትሩ በመጀመሪያው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማን በመዳኘት ሁለት የቢጫ ካርዶችን አሳይቶ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጠ ሲሆን በሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አራተኛ ዳኛ መሆን ችሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-4-3)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ሳልሀዲን ባርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ

አቤል ያለው  – አሌክስ ኦሮቶማ – አቡበከር ሳኒ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሶሆሆ ሜንሳህ 

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

ምንተስኖት አበራ – መሣይ ጳውሎስ 

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ሰለሞን ታፈሰ – ኄኖክ ድልቢ

እስራኤል እሸቱ