የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ተከፍቷል

የኢትዮጵያ ክለቦች የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከቅዳሜ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 30 ቀናት ክፍት ሆኗል።

ፊፋ ለአባል ሀገራቱ በሚያወጣው መሰረት የኢትዮጵያ የዝውውር መስኮት ከታኅሳስ 6-ጥር 6 (ከዲሴምበር 15 እስከ ጃንዋሪ 14) ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በቀራቸው ጥቂት ኮታ ተጫዋቾች ለማዘዋወር ጥረት እንደሚያደርጉ ይገመታል።

የውጪ ተጫዋቾችን ማዛወር የሚፈቀድበት የክረምቱ የዝውውር መስኮት ኦክቶበር 23 (ጥቅምት 13) የተዘጋ ሲሆን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ የሀገራችን የውስጥ ውድድሮች የተጀመሩት በጥቅምት ወር መጨረሻ መጀመራቸው ይታወሳል። እንደሌሎች ጊዜያት ሁሉ የዝውውር ጊዜያትን ያላማከለው የውድድር ስርዓታችን አሁን በተከፈተው የዝውውር መስኮት ተጫዋቾች ማስፈረም ክለቦችን ለኪሳራ የሚያጋልጥ ይመስላል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ይህ የዝውውር መስኮት ለኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከሚፈቀደው መስኮት ጋር ተመሳሳይ አካሄድን የሚከተል መሆኑ ነው። ይህም ማለት አንድ የፕሪምየር ሊግ ክለብ የሚያስፈርመውን ተጫዋች ሜዳ አስገብቶ መጠቀም የሚችለው የአንደኛው ዙር ከተጠናቀቀ በኋላ ነው። (ሊጉ ከበርካታ ተስተካካይ ጨዋታዎች ጋር ገና 6ኛ ሳምንት ላይ መገኘቱን፤ አሁን ባለው መርሐ ግብር መሠረት አንደኛው ዙር የሚጠናቀቀው መስኮቱ ከተዘጋ 23 ቀናት በኋላ የካቲት አንድ እንደሆነ ልብ ይሏል)።

ሆኖም በፌዴሬሽኑን የኢንተርናሽናል ዝውውሮች ተቆጣጣሪ የሆነው አቶ ሚኪያስ የሀገራችን የዝውውር ህግ ለክለቦች ጠቃሚ ጎን እንዳለውም ይገልፃል። ” የፊፋ የውጭ ተጫዋቾች ዝውውር መስኮት መከፈትን ተከትሎ አሁን ላይ የሚዘዋወሩ ተጫዋቾች ሁለተኛው ዙር እስከሚጀምር ምንም አይነት ጨዋታ ላይ መሳተፍ አይችሉም። ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት የመኖሪያ እና የስራ ፍቃድን የመሳሰሉ ህጋዊ መስፈርቶችን ለማሟላት በቂ ጊዜ ማግኘት መቻላቸው መልካም ጎኑ ነው።” ሲል አስተያየቱን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል።

በዝውውር መስኮቱ መከፈት ምክንያት ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል የኦኪኪ አፎላቢ አንዱ ነው። ናይጄርያዊው የ2010 የፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ከግብፁ ኢስማይሊ ጋር የነበረውን ኮንትራት በመቅደዱ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ይጠበቃል። ነገር ግን ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው መረጃ መሠረት ተጫዋቹ ወደ ኢትዮጵያ ክለብ ከተዘዋወረ ጨዋታ ለማድረግ በዲሲፕሊን ኮሚቴ የተጣለበትን እገዳ መጨረስ እና የገንዘብ ቅጣቱንም መጨረስ ይኖርበታል።

አምስት ተጫዋቾቾችን ማስፈረም በሚፈቅደው የኢትዮጵያ ዝውውር ከወላይታ ድቸ እና መከከየ ውጪ ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የውጪ ተጫዋቾችን በሰብስባቸው ይዘዋል።