ሪፖርት | አዳማ የዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን በመቐለ ላይ አስመዝግቧል

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ከንዓን ማርክነህ ጎልቶ በወጣበት የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከተማ መቐለ 70 እንደርታን 3-1 አሸንፏል።

አዳማ ከተማዎች በአምስተኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሽንፈት ካስተናገዳው ቡድናቸው ውስጥ አንዳርጋቸው ይልሀቅን እና ሙሉቀን ታሪኩን በሱለይማን መሀመድ እና ከንዓን ማርክነህ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። መቐለዎችም በተመሳሳይ በድቻ ከተረቱበት ጨዋታ ኤሌክስ ተሰማ እና ኦሲ ማዎሊን በማስቀመጥ ቢያድግልኝ ኤልያስን እና አማኑኤል ገብረሚካኤልን በመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ አካተዋል።

ተመጣጣኝ በሆነ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሙከራዎችን ለማስመልከት ረጅም ጊዜ ወስዶበታል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የግራ መስመር አማካዮች በመሆን በተሰለፉት የአዳማው በረከት ደስታ እና የመቐለው ሳሙኤል ሳሊሶ አቅጣጫ በማድላት ይሰነዘሩ የነበሩ የቡድኖቹ ጥቃቶች አደጋ በመፍጠር ደርጃ አስፈሪ መሆን አልቻሉም። በሂደት በተሻለ ሁኔታ ጫና ሲፈጥሩ ይታዩ የነበሩት አዳማዎች ወደ ግራ አድልቶ ሲንቀሳቀስ በነበረው ከንዓን እና በረከት መሀል ባመዘኑ ቅብብሎች ሰብረው ለመግባት ሲጥሩ ታይተዋል። የመጀመሪያው ሙከራም ከዚሁ ግራ መስመር በተገኘ ቅጣት ምት የተገኘ ነበር። ዳዋ ሁቴሳ በ21ኛው ደቂቃ ወደ ግራ መስመር ካደላው የርቀት ቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ኢቮኖ ተንሸራቶ በእግሩ አድኖበታል። ዋነኛ የጥቃት መሳሪያቸው የሆነው አማኑኤል ገብረሚካኤል እንቅስቃሴ ኃይል በተቀላቀለበት የአዳማ ተጫዋቾች አቀራረብ ስኬታማ መሆን ያልቻለው መቐለዎችም ለያሬድ ከበደ ከሚጥሏቸው ቀጥተኛ ኳሶች ነበር ወደ አዳማ ሳጥን ለመድረስ የሚሞክሩት። ሆኖም ንፁህ የግብ ዕድል ለብቸኛው አጥቂያቸው መፍጠር ተቸግረው ታይተዋል።


በሂደት የጨዋታው እንቅስቃሴ የሜዳ ላይ ግጭቶች ተበራክተውበት ከሙከራዎች ርቆ እና የረጅም ርቀት ቅጣት ምቶች ተደጋግመው እየታዩበት ለመቀጠል ተገዷል። በመሆኑም ወደ ማሰልቸቱ እየተጠጋ የመጣው ጨዋታ በስተመጨረሻ ነፍስ ዘርቶ ከነዚሁ በርካታ የቆሙ ኳሶች ጎሎችን ማግኘት ችሏል። በቅድሚያ 39ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ወደ ግራ መስመር ያደላ ቅጣት ምትን አሻምቶ ኢቮኖ እና የመቐለ ተከላካዮች በአግባቡ ሳይርቁት አዲስ ህንፃ አግኝቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ነገር ግን በተመሳሳይ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ የተሻገረው የመቐለዎች ቅጣት ምትም አዳማ ሳጥን ውስጥ አርፎ ባለሜዳዎቹ ሳያርቁት በሐይደር ሸረፋ አማካይነት ወደ ግብነት ተለውጧል። አስገራሚዎቹ የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግን አሁንም አንድ ጎል አስመልክተውናል። በጭማሪ ደቂቃ አዳማዎች በቀኝ መስመር በኩል በመልሶ ማጥቃት ሳጥን ውስጥ ገብተው ከንዓን ማርክነህ ከበረከት የተቀበለውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። በስምንቱ ደቂቃዎች የተቆጠሩት ሦስቱ ግቦችም አዳማን የ2-1 መሪ አድርገውት ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎች የተሻለ ተነቃቅተው ታይተዋል። በሱለይማን መሀመድ እና ቡልቻ ሹራ አማካይነት በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ያደረጓቸውም ሙከራዎች ኃይል ባይኖራቸውም ኢላማቸውን የጠበቁ ነበሩ። የጨዋታው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ግን እንደመጀመሪያው ግጭቶች የበዙበት አይሁን እንጂ ሙከራዎች እንደልብ የታዩበት አልነበሩም። በተለይም መቐለዎች በቅብብልም ሆነ በተሻጋሪ ኳሶች ወደ አዳማ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጓቸው ጥረቶች የተሳኩ አልነበሩም። አሰልጣኝ ገብረመድህንም በአማኑኤል እና ሚካኤል ምትክ ኦሲ ማዊሊን እና ዮናስ ገረመውን በማስገባት የማጥቃት ኃይላቸውን ለማጠናከር ቢሞክሩም በቡድኑ የማጥቃት ጥረት ውስጥ ከኋላ የሚታየው ክፍተት ለመልሶ ጥቃት ሲያጋልጠው ያጋለጠው ሆኗል።


ሱለይማን መሀመድ ከረጅም ርቀት ወደ ግብ አሻምቷት ከመረብ ለማረፍ ተቃርቦ ከነበረው ሙከራ ውጪ ከተጋጣሚ የተከላካይ መስመር ጀርባ ክፍተት ሲያገኙ ነፃነት የሚሰማቸው የአዳማ የመስመር አጥቂዎችም በከንዓን ማርክነህ እየተመሩ ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቃቸው አልቀረም። በተለይም በረከት ደስታ ፣ ቡልቻ ሹራ እና ዳዋን ቀይሮ የገባው ዱላ ሙላቱ በተደጋጋሚ ከኢቮኖ ፊት ያለውን ክፍተት ተጠቅመው ወደ ውስጥ የሚገቡባቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ፈጥረው ነበር። ሆኖም ስኬታማ የሆነው የቡድኑ ጥቃት የተፈጠረው 83ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። የመቐለ ተጫዋቾች የመከላከል ቅርፃቸውን ሳይዙ አዳማዎች በሰነዘሩት በዚህ ጥቃት ከንዓን ማርክነህ አሁንም እርጋታ በተሞላበት አጨረራረሱ ታግዞ የአዳማን መሪነት ወደ 3-1 ከፍ አድርጎታል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች መቐለዎች ልዩነቱን ለማጥበብ ቢጥሩም በጭማሪ ደቂቃ ሀይደር ሸረፋ ከሳሙኤል ሳሊሶ የተቀበለውን ኳስ በሚያስገርም መልኩ ዞሮ መቶት ኦዶንካራ በቅልጥፍና ካወጣበት የቡድኑ አደገኛ ሙከራ ውጪ ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በባለሜዳዎቹ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።