“በጨዋታው ደስተኛ ነኝ፤ ማሸነፋችንም ይገባናል።” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ በጃኮ አራፋት ብቸኛ ግብ አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ተከታዩን አስተያየት ሲሰጡ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ፍቅደኛ ባለመሆናቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻልንም።

ስለ ውጤቱ…

” ዛሬ ከትልቅ ቡድን ጋር ነበር የተጫወትነው። ተጫዋቾቼም ከትልልቅ ቡድኖች ጋር ስንጫወት ያላቸው የስነ ልቦና ደረጃ በጣም የሚገርም ነው። ለዛሬው ጨዋታ በፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ያሸንፍንበት ውጤት ትልቅ አስተዋጾ አድርጓልናል። ከምንም በላይ ግን ለዚህ ጨዋታ በደንብ ስንዘጋጅ ስለነበረ ውጤቱ ሙሉ ለሙሉ ይገባናል።”

ስለ ጨዋታው እና ስለ ቡድናቸው ደካማ ጎን…

” በዛሬው ጨዋታ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከተከላካይ እስከ አጥቂ ድረስ ጥሩ ለመጫወት ሞክረናል። ዛሬ በደንብ የተቀናጀ ቡድን ነው ያየሁት። ትንሽ ግን የተከፋሁት ብዙ ጎሎችን አስቆጥረን ማሸነፍ የምንችልበት ጨዋታ ስለነበረ ጎሎችን ባለማስቆጠራችን ነው እንጂ በጨዋታው ሂደት ደስተኛ ነኝ።”

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ስለተከተሉት አጨዋወት…

” ቅድም እንዳልኩት የተጫወትነው ከትልቅ ቡድን ጋር ነው። ግብ ካስቆጠርን በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ኋላ አፈግፍገን ተጫውተናል ይህ ደግሞ የሆነው ከጨዋታው ውጤት ይዞ ለመውጣት ከነበረን ጉጉት ነው። ”

ስለተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና…

” ኢትዮጵያ ቡና ብዙ ዓመት የተጫወትኩለት ክለብ ነው። በአሰልጣኝነትም በክለቡ አሳልፍያለው። ቡድኑ ጠንካራ ቡድን ነው። በፍጥነት ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ላይ እየደረሱ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ማድረግ የሚችሉ ተጫዋቾች የያዘ ቡድን ነው። ነገር ግን በዛሬው ጨዋታ እኛ በተሻለ ብልጫ ወስደን ተንቀሳቅሰናል። “