የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-2 መከላከያ

ዛሬ ከተካሄዱ አምስት የ6ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ጎንደር ላይ ፋሲል እና መከላከያ አቻ የተለያዩበትን ጨዋታ መጠናቀቅ ተከትሎ የቡድኖቹ አሰልጣኞች አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል።
” ጨዋታው በሁለታችንም በኩል መልካም እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ 

ስለ ጨዋታው…

” በሁለታችንም በኩል ጥሩ ጨዋታ ነበር። በኛ በኩል ከሌላው ጊዜ በተሻለ አጥቅተን ተጫውተናል ፤ በርካታ ዕድሎችንም ፈጥረናል። ከነርሱ ጋ በመልሶ ማጥቃት ሚመጡት ከባድ ኳሶች ነበሩ። ለግቦቹ መቆጠር አንዱ እንደዚሁ ከቅጣት ምት ፈጥነው ጀምረው ያገኙት ኳስ ነው። ሌላው ደግሞ በመልሶ መጥቃት ያገኙት ኳስ ነው። በመልሶ ማጥቃት ሌሎች ዕድሎችን ማግኝት ችለዋል እና በዛ በኩል መከላከያ የተሻለ ነበር።  በአጠቃላይ ግን ጨዋታው በሁለታችንም በኩል መልካም እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በርካታ የግብ ዕድሎችን በመፍጠራችን ግቡ ከዚህ በላይ መሆን ይችል ነበር ፤ በአጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነበር። ”

ስለዳኝነቱ…

” ግልጽ የሆኑ የሚታዩ ስህተቶች አሉ። ከፍፁም ቅጣት ምት ጋር የተያያዙ ግልጽ የሆኑ ፍፁም ቅጣት ምት የሚመስሉ አጋጣሚዎች ነበሩ። ያው እንግዲህ የዳኛው እይታ ከኔም ሆነ ከተመልካች እይታ ጋር ሊለያይ ይችላል። ዞሮ ዞሮ ግን ከዳኝነት ጋር የተያያዘ ብዙ ችግር አላየሁም። ሁለቱ ፍፁም ቅጣት ምቶች ግን በተለይ የሽመክት ጉግሣ እና እንዲሁ አንድ ሌላ ኳስ ግልጽ  የፍፁም ቅጣት ምት ነው የሚመስሉት ከዛውጭ ጥሩ ዳኝነት ነው። ”

ፋሲል ሁለት ነጥብ አጣ ወይስ አንድ ነጥብ አገኝ…?

” እንደ ነበረን የማጥቃት ሁኔታ ሁለት ነጥብ አጥተናል። ምክነያቱም በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። ከዕረፍት በፊት ብዙ ኳሶች ስተናል። የሙጂብ የጭንቀት ኳስ ሌሎች ሌሎች ከዛ ከነበረን ሙከራዎች አንፃር ብዙ ስተናል። በተቃራኒው እነሱም በመልሶ ማጥቃት  ያገኙት ከባባድ ኳስ ነበር። በተለይ በመጨረሻ ሰዓት ምንይሉ ወንድሙ አግኝቶ የሳተው ኳስ የሚያስቆጭ ነው። እኛም ጋ ሊያልቅ ሲል ግብ ጠባቂው ጨርፎ ያወጣው ኳስ የሚያስቆጭ ነው። ዞሮ ዞሮ ለኛ እንደጣልን ነው ምቆጥረው። ”

” ፋሲል ከነማ በሜዳው ከባድ እንደሆነ እናውቃለን ” ስዩም ከበደ – መከላከያ 

ስለ ጨዋታው…

” መጀመሪያ እኛ ወደዚህ ስንመጣ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ተሸንፈናል። በተጨማሪ ደግሞ ጥሩ በነበርንበት ሰዓት ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ጥለናል። ፋሲል ከነማ በሜዳው ከባድ እንደሆነ እናውቃለን። በዉጤት ደረጃ ደስተኛ ነኝ ፤ ሁለት እኩል በመውጣታችን። በተለይ በፋሲል የነበረው መነቃቃት እና ጫና  ለኛ ከብዶን ነበር። የጫናው መንስኤ እኛ እረፍት እንደተነጋገርነው ሁለት ለአንዱን አስጠብቀን ረጅም ጊዜ እንቆያለን ብለን አስበን ብዙ መጓዝ ከጀመርን 

የነሱ መውረድ ይመጣል ብለን አስበን ነበር። በዚህ አጋጣሚ  ከጠበቀነው ቀድመው  ግብ ማግኝታቸው አነሳስቷቸዋል። እኛም ጋር የነበረው  ቅንጅት ጥሩ አልነበረም። በመጨረሻም ግን ነጥብ ተጋርተን ወጥተናል። ”

ስለ ዳኝነት…

” እኔ የከፋ ነገር አላየሁበትም። ጥቃቅን ስህተቶች አሉ። ወደ ራሴ ስመለከተው ደግሞ ማንኛውም ጥቃቅን ስህተቶች ማስቀጠል ሲገባው ለምን አስቆመው የሚል ነው ። በተጨማሪ ግን እንደ እኔ የሚችለውን ነው ያደረገው። ለማንም ያዳለው ነገር የለም። ደጋፊው ተቃውሞ ውጤትን ከመፈለግ አኳያ ሊሆን ይችላል እንጂ ጎልቶ የወጣ ስህተት አላየሁም።”

መከላከያ ሁለት ነጥብ አጣ ወይስ አንድ ነጥብ አገኝ…

” የመጀመሪያ ምርጫችን ሦስት ነጥቡን አስጠብቆ መውጣት ነበር። አንድ አንድ ቴክኒካል አሳይመንቶች ሰጥቻቸው ነበር። ትንሽ ደቂቃ ብንሄድ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ። ግቡ ሲገባብን የፋሲል ከነማ መነሳሳት ጨመረ። የኛ ተጫዋቾች ደግሞ በጣም ወደ መከላከል ስላተኮሩ ጫና በውስጥ ነበርን። አንድ ነጥብ ለዋንጫም ላለመውረድም ወሳኝ ነው። አንድ ነጥብም ቢሆን በሰው ሜዳ የተገኘ ውጤት ስለሆነ ጥሩ ነው። “