ከፍተኛ ሊግ | የሦስተኛ ሳምንት የምድብ ለ ውሎ

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ሦስተኛ ሳምንት የተደረጉ አምስት ጨዋታዎች በሙሉ በመሸናነፍ ሲጠናቀቁ ወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን በሜዳቸው ኢኮስኮ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ሀምበርቾ ዱራሜ ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ድል ቀንቷቸዋል።

ወልቂጤ ላይ የተደረገው ወልቂጤ ከተማ እና ወላይታ ሶዶ ጨዋታ ከፍተኛ ጉሽሚያ የበዛበት ሆኖ አልፎል። በመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ በተጠናቀቀው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አስራ አምስት ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ተሽለው የነበሩት ወልቂጤዎች በ8ኛው ደቂቃ ተስፋዬ በቀለ ከርቀት መትቶ እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን በግንባሩ በመግጨት ባደረጉት የግብ ሙከራ ተነቃቅተው ታይተዋል። ሆኖም ወልቂጤዎች ከግብ ክልላቸው መራቃቸውን የተመለከቱት ወላይታ ሶዶዋች አቀራረባቸውን ከአጭር ቅብብል ወደ ረጅም ኳስ አጨዋወት በመለወጥ የወልቂጤን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መፈተን ችለው ነበር። በተለይም በ20ኛው ደቂቃ ሲሳይ ማሞ እና በ25ኛው ደቂቃ ዳግም ማትያስ እንዲሁም በ37ኛው ደቂቃ አስቻለው ስምዖን ያደረጉትን የግብ ሙከራ የግብ ጠባቂው የቤሌንጋ ኢኖህ ጥረት ታክሎበት ግብ ከመሆን ድንዋል። ወደ ኋላ አፈግፍገው የተጫወቱት ወላይታዎች በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ሲይደረግባቸው ቆይተዋል። በ30ኛው እና በ45ኛው ደቂቃ አህመድ ሁሴን በግንባሩ የገጨው ኳስ በግብ ጠባቂው ጥረት ሲድን በ38ኛው እና በ40ኛው ደቂቃ ተስፋዬ በቀለ ከርቀት የመታቸው ኳሶች የመጀሙሪያው በግቡ የላይኛው አግዳሚ እንዲሁም ሁለተኛው የቀኙን አግዳሚ ታከው ወጥተዋል።

ከዕረፍት መልስ ግብ ለማግባት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ መጓሻሸም በተስተዋለበት ጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ ተጨዋች በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። በ50ኛው ደቂቃ ወላይታ ሶዶ ሰለሞን ጌታቸው ከርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ሙከራ ያደረጉት ወልቂጤዎች በ52ኛው ደቂቃ እና 60ኛው ደቂቃ በተስፋዬ በቀለ እንዲሁም አህመድ ሁሴን የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።

በ63ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አብዱልከሪም ወርቁ ላይ በተሰራው ጥፋት ተጫዋቾች የእርስ በርስ ግጭት የተከሰተ ሲሆን ከዳኛ እይታ ውጭ ግብ ጠባቂው ምትኩ ታደሰ በድጋሚ አብዱልከሪምን በመማታቱ ምክንያት ግጭቱ ተባብሶ ለመቀጠል ተገዷል። የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ቤሌንጋ ኤኖህ ከግብ ክልሉ በመልቀቅ ወደ ተጋጣሚው ግብ ጠባቂ በመድረስ ለጥል በመጋበዙም ነገሩ ሳይባባስ የባለሜዳው አሰልጣኝ ደረጀ በላይ የራሳቸውን ተጫዋቾች በመቆጣት ማረጋጋት ችለዋል። በመቀጠልም የዕለቱ ዳኛ ለሁለቱም ግብ ጠባቂዎች የማስጠንቀቂያ ካርድ አሳይተው ጨዋታውን አስጀምረዋል።

በድጋሚ በ65ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ላይ በተሰራ ጥፋት ከተገኘው የቅጣት ምት አህመድ ሁሴን በግንባሩ የገጨውን ኳስ የሶዶ ተከላካዮች በቀላሉ ቢመልሱትም ከግብ ክላቸው ባለማራቃቸው የተገኘውን አጋጣሚ ተመስገን ደረሰ ወደ ግብ አክርሮ በመምታት የጨዋታውን ብቸኛ ግብ አስቆጥሯል። የአቻነት ግብ ፍለጋ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ተጠግተው የተጫወቱት ወላይታዎች በርካታ ሙከራዋች ቢያደርጉም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። በተቃራኒው ወልቂጤዎች የግብ ልዩነቱን ማስፋት የሚችሉበት አጋጣሚ በ79ኛው ደቂቃ አግኝተው የነበረ ቢሆንም አጥቂው አህመድ ሁሴን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በሌላኛው የጨዋታው ትዕይንት በ84ኛው ደቂቃ አራተኛው ዳኛ በቆመበት የሜዳ ክፍል የወላይታ ሶዶ ተጫዋቹ ሲሳይ ማሞ ተመታው ብሎ ቢወድቅም አራተኛ ዳኛው ምንም አይነት ጥፋት አልተሰራም በማለታቸው ፋዓድ አህመድ በዙሪያው ላሉት ባለሙያዎች በሚሰማ መልኩ አራተኛ ዳኛውን አፀያፊ ስድብ በመሳደቡ ምክንያት በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። በወቅቱ የወላይታ ሶዶ አሰልጣኝ ጳውሎስ ተጫዋቾቻቸውን በማረጋጋት ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ያደረጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይሰተናግድበት በወልቂጤ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የናሽናል ሲሚንት እና ሀምበርቾ ዱራሜ ጨዋታ እንግዶቹ ማሸነፍ ችለዋል። በጨዋታው ናሽናል ሲሚንት በ16ኛው ደቂቃ በጌቱ ረፌራ ግብ ቀዳሚ ቢሆንም በ36ኛው ደቂቃ ምንተስኖት ዳልጋ ለሀምበሪቾ የአቻነቱን ግብ ሲያስቆጥር የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቅቅ ሽርፍራፊ ደቂቃዋች ሲቀሩት ተስፋሁን የሀምበርቾን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። ከእረፍት መልስ በ78ኛው ደቂቃ የቀድሞ የንግድ ባንክ ተጫዋች በረከት አዲሱ ለአምብሪቾ ሦስተስኛውን ግብ አክሎ ጨዋታው በሀምበሪቾ ዱራሜ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


በሳምንቱ በበርካታ የግብ ልዩነት በተጠናቀቀው ሌላ ጨዋታ ኢትዮጽያ መድን በግብ ተንበሽብሾ ውሏል። በጨዋታው መድን በ27ኛው ደቂቃ ሂድር ሙስጣፋ ፣ በ52ኛው ደቂቃ አብዱልለጢፍ ሙራድ ፣ በ64ኛው ደቂቃ ሚካኤል ለማ ፣ በ75ኛው ደቂቃ ሰለሞን ወዴሳ እንዲሁም በ85ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ተጨማሪ ግብ የካ ክፍለ ከተማን 5-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በሌሎች ጨዋታዋች ዲላ ኢኮስኮን አስተናግዶ 75ኛው ደቂቃ ላይ አቤኔዜር ኦቴ ባገባው ብቸኛ ግብ በማሸነፍ መሪነቱን ማስጠበቅ ሲችል ነገሌ አርሲ በሜዳው በአዲስ አበባ ከተማ የሲሳይ ቶላ የ79ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 ተረቷል። እንግዳው ቡድን አአ ከተማ በነገሌ አርሲ የጨዋታ ሜዳ ላይ ቅሬታውን ለሶከር ኢትዮጵያ የገለፀ ሲሆን ሜዳው የአጥር ሽፋን የሌለው በመሆኑ ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመዋል። የከፍተኛ ሊግ አወዳዳሪ አካል ሜዳዎችን በተመለከተ በክረምቱ ጊዜ እንዲሁም ደግሞ በዕጣ አወጣጡ ስርዓት ወቅት ጠንከር ብሎ መናገሩ የሚታወስ ነው።