ፕሪምየር ሊግ | ሁለት የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተሸጋሽገዋል

የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሁለት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ የሰዓት እና የቀን ለወጥ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ይከናወናሉ። መጀመሪያው በወጣው መርሐ ግብር ቅዳሜ አምስት እንዲሁም እሁድ የጅማ አባ ጅፋርን ጨዋታ ሳይጨምር ሁለት ጨዋታዎች እንደሚስተናገዱበት ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ከነዚህም መሀል ሁለቱ ላይ ማስተካከያዎች ተደርገዋል። ማስተካከያው የተደረገው ጅማ አባ ጅፋር ከአል አህሊ ጋር እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም በሚያደርገው የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ምክንያት መሆኑም ታውቋል።

በዚህም መሠረት ቅዳሜ 10፡00 ላይ ይደረግ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ወደ 09፡00 የመጣ ሲሆን ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ አል አህሊዎች የመጨረሻ ልምምዳቸውን ያከናውናሉ። በተጨማሪም በቻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ ቀን እሁድ እንዲደረግ መርሐ ግብር ተይዞለት የነበረው የመከላከያ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ደግሞ ሰኞ 11፡00 ላይ እንዲደረግ ተወስኗል።