ቢሾፍቶ አውቶሞቲቭ ክለቡን እንደማያፈርስ ተረጋገጠ

በአምሀ ተስፋዬ እና ዳንኤል መስፍን

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ የሆነው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት የነበረ ቢሆንም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ውድድር እንደሚመለስ ታውቋል።

በብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ስር ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የሆነው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ በ2005 በስሙ ክለብ ካቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2008 በኦሮሚያ ሊግ ሲወዳደር የቆየ ሲሆን ከሁለት ዓመታት የአንደኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደግ ችሏል። ክለቡ በበጀት እጥረት ምክንያት ምዝገባ ሳያከናውን ቆይቶ የመጀመርያዎቹ ሦስት ሳምንታት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች አልፈውት እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ክለቡ እንደሚፈርስና በሌላ ክለብ እንደሚተካ ሲነገር ቢቆይም ከክለቡ የበላይ ጠባቂ ኮሎኔል ተክሉ ጸጋዬ ባገኘነው መረጃ መሠረት ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ እንደክለብ ይቀጥላል። ለከፍተኛ ሊጉ መመዝገቢያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ መክፈሉንና በቀጣይ ጊዜያት በፋይናንስ ለመጠናከር የገቢ ማሰባሰብያ ስራዎች ለመስራት እንደታሰበም ተናግረዋል።

በከፍተኛ ሊግ በማዕከላዊ ደቡብ ምዕራብ ምድብ የተደለደለው ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ከአምናው ስብስቡ በብዙ መልኩ ለውጥ በማድረግ  የተዋቀረ ሲሆን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን ኃላፊነቱን የተረከበው አሰልጣኝ ፍሬው ኃ/ገብርኤል ነው። አሰልጣኝ ፍሬው በቢሸፍቱ ከተማ የሚገኙ በርካታ ታዳጊዎችን ሰብስቦ በማሰልጠን አሁን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ እየተጫወቱ ያሉ ተጫዋቾች በማውጣት መልካም ስም ያተረፈ ሲሆን በተለይ በ2008 የደደቢት የሴቶች ቡድኑ በመያዝ የሊጉ ቻምፒዮን በማድረግ የውድድር ዓመቱ ኮከብ አሰልጣኝ በመሆን መመረጡ ይታወቃል። ከደደቢት የሴቶች ቡድን ጋር ከተለያየ በኋላ የሲዳማ ቡና የሴቶች ቡድንን በመያዝ ሲያሰለጥን መቆየቱ ይታወሳል። የእርሱ ረዳት በመሆን የሚያገለግለው የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስመጥር ተጫዋች ጌታቸው ካሳ (ቡቡ)  ሲሆን  ደጉ ደሳለኝ ሌላኛው ም/አሰልጣኝ ነው።

ከቡድኑ ጋር ባሳለፍነው ዓመት አብረው ከነበሩ ስብስብ መካከል ሚልዮን ብሬ ፣ ማንደፍሮ ቢረዳ ፣ ታሪኩ እሸቴ እና ፀጋ ዓለማየሁን ከቡድኑ ጋር አብረው ሲቆዩ በርካታ አዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

አዳዲስ ፈራሚዎች

ግብ ጠባቂዎች፡ ዘውዱ መስፍን፣ ወርቅነህ ዲባባ እና ሐብታሙ ሰለሞን

ተከላካዮች፡ መግቢያነህ አሳዬ ፣ ዳዊት ሞገስ ፣ መሀመድ ሁሴን ፣ ይደነቁ የሺጥላ እና ዘሪሁን ዐቢይ

አማካዮች፡ ሰለሞን ከበደ ፣ ተዘራ መንገሻ ፣ ሚካኤል ወንድሙ ፣ ዳግም አስቻለው እና ወግደረስ ታዬ

አጥቂዎች፡ ኢሳይያስ ዓለምሸት፣ ሲሳይ አማረ ፣ ቢኒያም ጌታቸው እና ወንድማገኘው አብሬ


ከዚህ በተጨማሪ ቴዎድሮስ ምንአለ ፣ አለማየሁ ታአምሩ ፣ ተስፍ በቀለ እና ዳዊት ከበደ የተሰኙ ተጫዋቾችን ቢሾፍቱ ከተማ ከሚገኙ የታዳጊ ቡድኖች በመመልመል በቡድኑ ውስጥ ማካተት ችለዋል።

ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ህልውናው መረጋገጡን ተከትሎ በከፍተኛ ሊጉ የመጀመርያ ጨዋታውን በአራተኛ ሳምንት ከቡታጅራ ከተማ አልያም በአምስተኛ ሳምንት በሜዳው ከሻሸመኔ ከተማ ጋር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።