ኦኪኪ አፎላቢ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ ይመለስ ይሆን ?

ውሉ ሳይጠናቀቅ በስምምነት ከግብፁ ኢስማይሊ ጋር የተለያየው የቀድሞው የጅማ አባ ጅፋር አጥቂ ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በጥር ወር አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስበት ዕድል የሰፋ ነው።

ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት የመጀመሪያ ዓመቱ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር የሊጉ ቻምፒዮንነት ክብርን በማግኘት እና ኮከብ ጎል አስቆጣሪ በመሆንም ጭምር ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ናይጄርያዊ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ዘንድሮ የግብፁን ኢስማይሊን መቀላቀል ችሎ ነበር። ሆኖም በተወሰኑ ጨዋታዎች ካልሆነ በስተቀር በግብፅ የነበረው ቆይታ የተረጋጋ ያልሆነለት ኦኪኪ ከወራት በፊት ነበር ከደሞዝ ክፍያ እና በቂ የመጫወት ዕድል ካለማግኘት ጋር ተያይዞ ከክለቡ አመራሮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ያደረገው ድርድር ተሳክቶለት ባሳለፍነው ሳምንት ከግብፁ ክለብ ጋር በስምምነት በመለያየት መልቀቂያውን መውሰድ ችሏል።

አሁን በሀገሩ ናይጄሪያ የፀጉር አቆራረጥ ስታይሉን በመቀየር ከቤተሰቦቹ ጋር የዕረፍት ጊዜውን እያሳለፈ የሚገኘው ኦኪኪ እንግሊዛዊ ህጋዊ ኤጀንቱ ወደ ሌላ ሀገር ሄዶ እንዲጫወት ፍላጎት ያለው ቢሆንም ኦኪኪ ግን ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው እየተነገረ  ይገኛል። ኦኪኪ ዳግመኛ  ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስ ከሆነ መቐለ 70 እንደርታ የእርሱ ጥብቅ ፈላጊ ሆኖ እንደቀረበ ሲነገር ይህ የሚሳካ ከሆነ ከቀድሞ አሰልጣኙ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር አብሮ የመስራት ዕድል የሚያገኝ ይሆናል። ሌላው የኦኪኪ ፈላጊ ክለብ ሆኖ የቀረበው በአሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ የሚመራው አዳማ ከተማ እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል።

ኦኪኪ አፎላቢ የተጫዋችነት ህይወቱን በሀገሩ ክለብ ሰንሻይን ስታርስ ጀምሮ ወደ አርጀንቲናው ታሌሬስ ዲ ኮርዶባ ከሄደ በኋላ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ጥሩ ጊዜ አሳልፎል። የተጫዋቹ ቀጣይ ማረፊያም በጥር ወር አጋማሽ የሚታወቅ ይሆናል።