ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ኢትዮጵያ በድጋሚ ለምን መጣ ?  

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኢትዮጵያ ቡናን ለቆ በጃፓን 4ኛ ዲቪዝዮን ለሚወዳደረው ቴጌቫያሮ ሚያዛኪ ፊርማውን ያኖረው ናይጄሪያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ልምምድ እየሰራ ይገኛል።

የቀድሞው የኢትዮዽያ ቡና አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በአሁኑ ሰዓት ወደ ኢትዮጵያ ዳግመኛ መምጣቱን ተከትሎ እና ከኢትዮጵያ ቡና እግርኳስ ክለብ ጋር አብሮ ልምምድ እየሰራ የመሆኑ ጉዳይ ተጫዋቹን በድጋሚ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ልናየው ይሆን? የሚል ጥያቄን ያስነሳ ሆኗል።

ሆኖም ናይጄሪያዊ አጥቂ ሳኑሚ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ምክንያት ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ሳይሆን የጃፓን ሊግ የመጀመርያው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ የዕረፍት ጊዜውን ለማሳለፍ እና በኢትዮጵያ ቡና ያልተከፈለውን ደሞዝ ለመቀበል እንደሆነ ለማወቅ ችለናል። ለአስር ቀናት በአዲስ አበባ በሚኖረው ቆይታው እግረ መንገዱን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ልምምድ እየሰራ የሚቆይ ሲሆን ከቀናት በኋላ ወደ ጃፓን የሚያቀና ይሆናል።

የእግርኳስ ህይወቱን በሌጎሱ ዩንየን ባንክ ክለብ የጀመረው ሳኑሚ በ2003 በቡልጋርያዊው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የወቅቱ አሰልጣኝ ዮርዳን ስቶይኮቭ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ እስካለፈው የውድድር ዓመት ድረስ በሀገራችን ቆይታ አድርጓል። አጥቂው ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለ ሲሆን በ2006 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በ2007 የደደቢት ቆይታው ደግሞ በ22 ግቦች በሊጉ ታሪክ የመጀመርያው የውጪ ዜጋ የሆነ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረስ ችሏል።