ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሁለት የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታዎች ተጀምሯል። መከላከያ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ሀዋሳ ከተማም ከሜዳው ውጪ አሸንፏል።

በ8:00 ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በእንግዳው ቡድን ሀዋሳ አሸናፊነት ተጠናቋል። ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሀዋሳዎች በረጃጅም ኳሶች የተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ የግብ እድል ሲፈጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በ17ኛው ደቂቃ ነፃነት መና እና በ20ኛው ደቂቃ መሠረት መሰለ ያደረጓቸውት የግብ ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

በ23ኛው ደቂቃ ነፃነት መና በረጅሙ የተሻገረላትን ኳስ ወደ ግብነት በመለወጥ ሀዋሳን ከተማን አሸናፊ የምታደርግ ግብ አስቆጥራለች። ከግቡ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተለይ ተቀይራ ወደ ሜዳ በገባችው መሣይ ተመስገን ጥረት ያደረጉት የግብ ሙከራ ሳይሳካ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ሙሉ በሙሉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የጨዋታ ብልጫን ቢወስድም ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል። በአጭር ቅብብል የሀዋሳን የግብ ክልል ሲፈትሹ የነበሩት ኤሌክትሪኮች በሰሚራ ከማል፣ በመሣይ ተመስገን፣ ወርቅነሽ መልሜላ እና ለምለም ወልዱ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ወደ ግብነት ሳይለወጡ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው 14ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ እስራኤል ከተማ በጉዳት ተቀይራ ወጥታለች።

በ10:00 መከላከያ ከአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በመከላከያ ፍፁም የበላይነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ መከላከያዎች ብልጫን ያሳዩ ሲሆን በ11ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው የመታችውን ኳስ የግቡ ብረት ለትሞ ሲወጣ በ18ኛው ደቂቃ ኤልሳቤጥ ብርሃኑ ያደረገችው ሙከራ በግብ ጠባቂዋ ከሽፎባታል።

ጨዋታው በመከላከያ ጫና ቀጥሎ በ29ኛው ደቂቃ መዲና ዐወል በሁለት ተከላካይ መሐል አልፋ ወደ ግብ አክርራ የመታችው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ ጦሩ ቀዳሚ ሆኗል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ እመቤት አዲሱ ከሳጥን ውጭ የመታችው ጠንካራ ኳስ ግብ ጠባቂዋ በእግሯ ለማራቅ ስትሞክር እዛው የቀረውን ኳስ ኤልሳቤጥ ብርሀኑ በፍጥነት ደርሳ በግንባሯ በመግጨት ጎል አስቆጥራ በመከላከያ 2-0 መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ሰዓት ለማባከን በሚመስል መልኩ ለበርካታ ጊዜ መሬት ላይ በመውደቅ ጨዋታው ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥ የነበረ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በርካታ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል። በተለይም ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ቤዛ ታደሰ ያደረገቻቸው ሙከራዎች እንዲሁም በ70ኛው ደቂቃ አስራት ዓለሙ አክርራ ወደ ግብ መትታ ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የወጣባት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም በ88ኛው ደቂቃ ኤልሳቤጥ ብርሀኑ ለራሷ ሁለተኛውን ለቡድኗ ሶስተኛውን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 3-0 ተጠናቋል።

5ኛ ሳምንት
ዓርብ ታኅሳስ 12 ቀን 2011
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-1 ሀዋሳ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ 0-3 መከላከያ
እሁድ ታኅሳስ 14 ቀን 2011
ጌዴኦ ዲላ 09:00 ጥሩነሽ ዲባባ
ድሬዳዋ ከተማ 09:00 ጥረት ኮርፖሬት
አርባምንጭ ከተማ 09:00 ኢትዮ ንግድ ባንክ
ሰኞ ታኅሳስ 15 ቀን 2011
ቅዱስ ጊዮርጊስ 09:00 አዳማ ከተማ
_____