ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ስሑል ሽረ

ከቅዳሜ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በስተመጨረሻ የሚደረገውን የሀዋሳ እና ሽረ ጨዋታ እኛም በዳሰሳችን የምንመለከተው የመጨረሻው የነገ መርሀ ግብር ይሆናል።

የሀዋሳው ሰው ሰራሽ ሜዳ ከደቡብ ፖሊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በመቀጠል ሀዋሳ ከተማ እና ስሐል ሽረን የሚያገናኘውን ጨዋታ 10፡00 ላይ ያስተናግዳል። የሊጉ መሪዎች በተመልካቾች ሁከት ሳቢያ በዝግ ስታድየም ከተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ አንድ ነጥብ ይዘው በመመለሳቸው በሁለት ነጥብ ልዩነት አንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል። እስካሁን የስድስቱንም ሳምንታት ጨዋታዎች በማድረግ ብቸኛ የሆኑት ሀዋሳዎች ተከታዮቻቸው በተስተካካይ ጨዋታዎች እንዳይደርሱባቸው ከነገው ጨዋታም ሙሉ ነጥብ ይዘው መውጣት ይጠበቅባቸዋል። የመጀመሪያ የሊግ ግባቸውን ሳምንት በሜዳቸው ሲዳማን ሲገጥሙ ያገኙት ሽረዎች ሙሉ ሦስት ነጥቦችን የሚገኙበትን የሊግ ጨዋታ ግን ገና በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። አዲስ አዳጊዎቹ ሽረዎች  ከአቻ ውጤቶች ባገኟቸው አራት ነጥቦች ነው በሊጉ ከደደቢት እና ደበብ ፖሊስ ብቻ የበላይ ሆነው 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት።

ሀዋሳ ከተማ አሁንም በቅጣት አይቮሪኮስታዊውን ተከላካይ ያኦ ኦሊቨርን የማያሰልፍ ሲሆን የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሀንስ በጉዳት የመሰለፍ ያለመሰለፍ ጉዳይ አለየለትም። ሆኖም አንጋፋውን ተጫዋች አዳነ ግርማን ከአራት ጨዋታ ቅጣት መልስ የሚደርስ ሲሆን ዮሃንስ ሴጌቦም በተመሳሳይ ከጉዳት የሚመለስ ተጫዋች ይሆናል። በቅጣት ምንም ተጫዋች የማያጣው ስሑል ሽረ ደግሞ ጉዳት ገብረመድህንን የማይጠቀም ይሆናል።

የአጨዋወት ለውጡ ያዋጣው የሚመስለው ሀዋሳ ከተማ ነገም በቀጥተኛ አቀራረብ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በተለይም ከሁለቱ መስመሮች ወደ እስራኤል እሸቱ የሚላኩ ኳሶች የሱሑል ሽረ የመሀል ተከላካዮች ዋነኛ ትኩረት መሆናቸው አይቀርም። የአዳነ መመለስም የሀዋሳዎችን ጉልበት የሚጨምረው ይሄናል። ቡድኖቹ አምስት አማካዮችን ከመጠቀማቸው አንፃር ግን ተሻጋሪ ኳሶቹ ወደ ሽረ የአደጋ ክልል ከመድረሳቸው በፊት ከበድ ያለ ፍልሚያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ይገመታል። በአንፃሩ ሽረዎች ጥንቃቄ አዘል አካሄድን የመምረጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው። በመሆኑም ለብቸኛ አጥቂያቸው ሳይሆን ለተከላካይ መስመራቸው የቀረበ የመሀል ክፍል ቅርፅ ሊይዙ ይችላሉ። ሆኖም ቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ባላቸው አማካዮቹ በኩል የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር መንቀሳቀሱ የማይቀር ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሀዋሳ ከተማ እና ስሐል ሽረ በነገው ጨዋታ የፕሪምየር ሊግ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ይጀምራሉ።

– ሀዋሳ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልገጠመው ሲሆን በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ምንም ግብ አላስተናገደም።

– ስሑል ሽረ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግብ ያላስቆጠረ ሲሆን በሦስቱ ደግሞ ግብ ሳያስተናግድ መውጣት ችሏል።

ዳኛ

– ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻን ከመቐለ 70 እንደርታ ባገናኘው ጨዋታ ተመድቦ ሦስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን የመዘዘው  ኢሳያስ ታደሰ የነገውን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ ( 4-2-3-1) 

ሶሆሆ ሜንሳህ

ዳንኤል ደርቤ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ደስታ ዮሃንስ

አዳነ ግርማ  – መሣይ ጳውሎስ

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ሰለሞን ታፈሰ – ኄኖክ ድልቢ

እስራኤል እሸቱ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት  – ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ – ክብሮም ብርሀነ

ንሰሀ ታፈሰ – ኄኖክ ካሳሁን

ልደቱ ለማ – ጅላሎ ሻፊ – ኪዳኔ አሰፋ

ሚድ ፎፋና