ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ| ጅማ አባጅፋር ለነገው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን አከናወነ

በ2018/19 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመካተት በሚረዳው አንደኛ ዙር መርሐ ግብር ባሳለፍነው ሳምንት ወደ አሌክሳንድሪያ ተጉዞ በግብፁ አል አህሊ 2-0 የተሸነፈው ጅማ አባ ጅፋር ነገ ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ዛሬ ጠዋት የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

ከሜዳ ውጭ ባለው አስተዳደራዊ ችግር ያልተረጋጋው ጅማ አባ ጅፋር የሁለት ጎል ልዩነቱን በመቀልበስ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት የሚጠብቀውን ጠንካራ ፈተና ለመወጣት ከካይሮ መልስ በተለያዩ ሜዳዎች ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ዛሬ ጠዋት ላይ የመጨረሻውን ልምምዱን በጥሩ ሁኔታ አጠናቋል። ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ ልምምድ ቢጀምርም ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ ያላገገመ በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ የተቀሩት የቡድኑ ተጫዋቾች በሙሉ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ መመልከት ችለናል።

የቡድኑ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ ስለ ነገው ጨዋታ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ክፍተቶቻቸውን አሻሽለው ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ገልጸዋል።” በመጀመርያው ጨዋታ እነሱ በመስመር ማጥቃት ላይ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ። እኛ የምናገኛቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀምም ሆነ ኳሱን በመቆጣጠር ረገድ ጥሩ አልነበርንም። ነገ ይህን ክፍተታችንን አሻሽለን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን። ደጋፊውም እገዛ እንዲያደርግልን እንፈልጋለን። ” ብለዋል።

ለጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት አል አህሊዎች ሐሙስ እኩለ ለሊት ላይ በርከት ያሉ የልዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ አዲስ አባባ የገቡ ሲሆን የመጨረሻ ልምምዳቸውን ከዛሬው የኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚሰሩ ይሆናል።

ነገ 10:00 የሚደረገውን ወሳኝ ጨዋታ ሶማሊያዊያኑ መሐመድ ሐጂ (ዋና)፣ ሐምዛ አብዲ (ረዳት1) እና አብዲ መሐመድኑር (ረዳት 2) ሲመሩት ኮሚሽነር ከሊቢያ ተመድበዋል።