የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ጎበኙ

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኙ የስፖርት መሠረተ ልማት ስፍራዎች በምክትል ከንቲባው የሚመራው የልዑክ ቡድን ከትላት ጀምሮ ሲጎበኙ ውለዋል። 

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጅነር) የአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት እና ባህልና ቱሪዝም የቢሮ ኃላፊዎች፣ የክለብ ደጋፊዎች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ነበር ከ08:00 ጀምሮ መጎብኘት የተጀመረው። የጉብኝታቸው የመጀመርያ ስፍራ ከ1992 ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ሰፊ የእድሳት ስራ ሲሆን አብዛኛው ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። ለስቴዲየሙ የተለየ ውበት የፈጠረት ሙሉ የተመልካች መቀመጫ ክፍል የወንበር ግጣሙ ተጠናቆ የተቀሩት ስራዎች ለምሳሌ የመሮጫ ትራኩ የመጀመርያው የኮንክሪት ንጣፉ ተጠናቆ መም (ትራክ) የማልበስ ስራው በጅማሮ ላይ ሲገኝ የስታዲየሙን ሙሉ ክፍል ጣርያ የማልበስ ስራ የብረት ግጣሙ አልቆ ጣሪያው ማልበስ በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል። በአጠቃላይ አብዛኛው ስራዎቹ እየተገባደደ እንደሆነና ሚያዚያ ወር መጀመርያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር፤ እስካሁን ለእድሳት እና ግንባታው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደወጣበትም ሰምተናል። 

በመቀጠል ክቡር ምክትል ከንቲባው ከራስ ኃይሉ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራ ጉብኝታቸው በኋላ ያመሩት በአዲስ አበባ ከሚገኙ ስታዲየሞች ሁሉ ተወዳዳሪ ወደሌለው በመንግስት ሙሉ ወጪ ሽፋን ተደርጎለት ከ60 ሺህ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም እንዲኖረው ታስቦ ግንባታው ከሦስት አመት በፊት ወደጀመረው ቦሌ አካባቢ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ብሔራዊ ስቴዲየም ነበር። የስቴዲየሙ የግንባታ ቁመናው የተጠናቀቀ ሲሆን የመጫወቻ ሜዳውን እና የመሮጫ ትራኩን ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ለማየት ችለናል። ከ65% በላይ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን እስካሁን ከፍተኛ የሆነ ወጪ እየወጣበት ሲገኝ ግንባታውን በፍጥነት በማጠናቀቅ በዋናነት በ2020 ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ለማድረስ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በመጨረሻም ምክትል ከንቲባው ተዟዙረው በተመለከቱት ነገር መደሰታቸውን በመግለፅ ግንባታቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ መመርያ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች የስፖርት መሠረተ ልማቶችን በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት እንደሚገነቡ እና የተወሰዱ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን ለማስመለስ እንደታሰበ ተናግረዋል።

አስቀድሞ ከጠዋት ጀምሮ የጉብኝታቸው አካል ይሆናሉ ተብለው መርሐ ግብር የወጣላቸው በተለይ የአቃቂ ስታዲየም ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ስታዲየሞችን በተለያዩ ምክንያቶች እና በፕሮግራም መጣበብ የተነሳ በቅርቡ ለመጎብኘት ቀጠሮ እንደያዙ በመግለፅ ሳይጎበኙ ቀርተዋል።