ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | አዳማ ከተማ የሊጉ አናት ላይ ተቀመጠ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን አምስተኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በአደማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የሊጉ መሪ መሆን ችሏል።

ኳስን ተቆጣጥሮ በመጫወት ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ እንቅስቃሴቸው በጎል ሙከራ ያልተጀበ በመሆኑ ጥረታቸው ትርጉም አልባ ይሁን እንጂ ከአዳማዎች የተሻሉ ነበሩ። አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የፊት አጥቂዎቻቸው ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም የተሻሉ በመሆናቸው በ10ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ የሰራችውን ስህተት ተከትሎ አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ አዳማዎችን መሪ ማድረግ ስትችል ብዙም ሳይቆይ ተመሳሳይ ስህተት የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ፈፅማ በ13ኛው ደቂቃ ዮዲት መኮንን ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች። ጥሩ ለመጫወት እየተንቀሳቀሱ ለነበሩት ፈረሰኞቹ በሁለት አጋጣሚ የግብ ጠባቂዋ ስህተት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ የተነቃቁት አዳማዎች ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ተጠቅመው ጫና ፈጥረው ቢጫወቱም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። በዕለቱ ጥሩ ትንቀሳቀስ የነበረችው ሶፋኒት ተፈራ በ36ኛው ደቂቃ ግሩም ጎል ከሳጥን ውጭ ለጊዮርጊስ አስቆጥራ የመጀመርያው አጋማሽ በአዳማ 2-1 መሪነት ተገባዷል።

ከመጀምርያው አጋማሽ ተመሳሳይ ሆኖ በቀጠለው ሁለተኛው አጋማሽ እንደተለመደው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን በጥሩ ሁኔታ አደራጅተው ይጫወቱ እንጂ ጠንካራ የሚባል የጎል ሙከራ ማድረግ ላይ ይቸገሩ ነበር። በአንፃሩ አዳማዎች በተሻለ ሁኔታ ሰናይት ቦጋለ በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሴናፍ ዋቁማ የምትጥላቸው ኳሶች አደጋ ሲፈጥሩ ታይተዋል። 81ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን መስከረም ካንኮ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በአዳማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ ድሉን ተከትሎ በ13 ነጥቦች የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

የመጀመርያ አምስት ደረጃ የያዙ ቡድኖች

ደረጃ. ክለብ ተጫ (ልዩ) ነጥብ

1. አዳማ ከተማ 5 (+6) 13
2. ንግድ ባንክ 5 (+6) 13
3. መከላከያ 5 (+5) 12
4. ጌዴኦ ዲላ 5 (+4) 12
5. ሀዋሳ ከተማ 5 (+5) 8