ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ሽረ ላይ የሚደረገው የስሑል ሽረ እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ ላይ ቀጣዮቹን ነጥቦች ልናነሳ ወደናል።

የመጀመሪያ የሊግ ድሉን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ስሑል ሽረ እንደተጠበቀው ያልሆነው መቐለ 70 እንደርታን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 09፡ 00 ላይ ይጀምራል። 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረዎች በአቻ ውጤት ከጨረሷቸው አራት ጨዋታዎች ውጪ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ4-0 በሀዋሳ ከተማ ደግሞ 6-1 ሰፋፊ ሽንፈቶች ገጥሟቸዋል። ወደ ሊጉ ወገብ የተንሸራተተው መቐለም በሁለት ድሎች ሊጉን ቢጀምርም በቀጣይ ካደረጋቸው ሁለት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ነጥብ ማሳካት ሳይችል ነበር ሳምንት ከጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋራው። በመሆኑም ጨዋታው በመሸናነፍ ከተጠናቀቀ ከመሪዎቹ እየራቀ ለሚገኘው መቐለ የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ፤ ካሁኑ በአደጋው ዞን ውስጥ ለተቀመጠው ስሑል ሽረ ደግሞ የመጀመሪያ የሊጉ ድል ሆኖ ይመዘገባል።

በበርካታ ጉዳቶች እየተጠቁ ያሉት ሽረዎች በሀዋሳው ጨዋታ የቀይ ካርድ ሰለባ ከሆነው ዲሜጥሮስ ወልደስላሴ ቅጣት በተጨማሪ ንስሃ ታፈሰ ፣ መብራህቶም ፍስሃ ፣ ደሳለኝ ደባሽ እና ሠለሞን ገብረመድህንን በጉዳት ምክንያት የሚያጡ ሲሆን የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው መቐለ 70 እንደርታ ግን ያለምንም ጉዳት እና ቅጣት ዜና ወደ ሽረ አምርቷል።

በጨዋታው ሁለቱም ተጋጣሚዎች አጥቅተው በመጫወት ክፍተቶችን ለማግኘት መጣርን ቀዳሚ ምርጫቸው አድርገው እንደሚገቡ ይጠበቃል። ኳስ መስርተው መጫወትን ሚያዘወትሩት ሽረዎች ተጋጣሚያቸው የመስመር ተከላካዮቹን እምብዛም በማጥቃት ላይ የማያሳትፍ እና ሁለት የተከላካይ አማካዮችን የሚጠቀም ከመሆኑ አንፃር ወደ አደጋ ክልል ለመግባት ሊቸገሩ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው። በተሻለ ፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ የሚያስችሉ ፈጣን አማካዮች ያሏቸው መቐለዎች ደግሞ በዋነኝነት ከፊት አጥቂው ጀርባ የሚሰለፉትን እነዚህን ተጫዋቾች መሰረት ባደረገ የማጥቃት ሽግግር የሽረን የኋላ መስመር እንደሚፈትኑ ይገመታል። በጥቅሉ ሁለቱም ቡድኖች በቅርብ ጨዋታዎች በማጥቃት ፍላጎት ውስጥ ሆነው ወደ ፊት ሲሄዱ ከኋላ ክፍተቶችን በሚፈጥሩባቸው አጋጣሚዎች ሲቸገሩ መታየታቸው በነገው ጨዋታ ይህ ደካማ ጎናቸው አንዳቸውን ለሌላኛቸው ማጋለጡ የሚቀር አይመስልም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሉጉ የሚገናኙበት የመጀመሪያ ጨዋታቸው ይሆናል።

– ስሑል ሽረዎች ሜዳቸው ላይ ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤት ሲለያዩ ሦስቱ ጨዋታዎች ያለግብ የተጠናቀቁ ነበሩ።

– በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ የቀናው መቐለ 70 እንደርታ ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ ድል ሲያደርግ በሁለቱ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ጨዋታው ከከፍተኛ ሊጉ ላደገው ባህሩ ተካ ሦስተኛ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታው ይሆናል። አርቢትሩ ከዚህ ቀደም መከላከያ እና ወልዋሎን እንዲሁም ደቡብ ፖሊስ እና ባህርዳርን ባገናኙት ጨዋታዎች ላይ ተመድቦ የዳኘ መሆኑ ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ሰንደይ ሮቲሚ

አብዱሰላም አማን – ዘላለም በረከት – ኄኖክ ብርሀኑ – ሙሉጌታ ዓንዶም

ንሰሀ ታፈሰ – ኄኖክ ካሳሁን

ልደቱ ለማ – ጅላሎ ሻፊ – ኪዳኔ አሰፋ

ሚድ ፎፋና


መቐለ 70 እንደርታ (4-2-3-1)

ፍሊፔ ኦቮኖ

አሞስ አቼምፖንግ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – አንተነህ ገብረክርስቶስ

ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ሐይደር ሸረፋ – ሳሙኤል ሳሊሶ

ኦሰይ ማውሊ