ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ሀዋሳ እና አዳማ በሜዳቸው ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ሲካሄዱ በክልል ከተሞች በተደረጉ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሲያሸንፉ ጥረት ከአርባምንጭ ነጥብ ተጋርተዋል።

አዳማ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማን ከጌዲኦ ዲላ ያገናኘውን ጨዋታ ባለሜዳው አዳማ ከተማ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ልማደኛዋ አጥቂ ሴናፍ ዋቁማ በ25 እና 85ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረቻቸውን ጎሎች መጠን ስድስት ስታደርስ የመስመር አጥቂዋ ሰርካለም ጉታ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛውን ግብ ለአዳማ ማስቆጠር ችላለች። አዳማ ድሉን ተከትሎ ሊጉን በግብ ልዩነቶች መምራቱን ቀጥሏል።

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ድል ማስመዝገብ ችሏል። በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ እጅግ ከባድ ፀሐይ ታጅቦ ጨዋታው እንደመደረጉ በሜዳ ላይ የተፈለገው እንቅስቃሴ መመልከት ሳይቻል ቀርቷል። የግብ እድሎችን በመፍጠሩ ረገድ እጅግ የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳዎች ጎል ለማግኘት ብዙ ደቂቃዎች መጠበቅ አላስፈለጋቸውም። 8ኛው ደቂቃ ላይ የግል ጥረቷን አክላ ወደ ሳጥን ኳስ እየነዳች የገባችሁ የመስመር ተጫዋቿ ካሰች ፍሰሀ ግብ አስቆጥራ ሀዋሳን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች። ምላሽ ለመስጠት ጥረት ያደረጉት ጊዮርጊሶች በብርሀን ኃይለሥላሴ መልካም አጋጣሚን ቢያገኙም ፍሬ ማፍራት ያልቻሉ ሲሆን በአንድ ሁለት ቅብብል ጥሩ ኳስ የደረሳት ዳግማዊት በተከላካዮቹ እና በግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ ቀድሞ ከሽፎባታል። 29ኛው ደቂቃ ላይ በዳግማዊት ሰለሞን አማካኝነት ያስቆጠሩት ጎልም ከጨዋታ ውጭ ተብሏል፡፡ ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ በርከት ያሉ እድሎችን በመፍጠር የተወሰደባቸውን ብልጫ ያስመለሱት ሀዋሳዎች በ34ኛው ደቂቃ ላይ ርብቃ ጣሰው በረጅሙ የላከችላትን ኳስ አጥቂዋ ነፃነት መና ወደ ግብነት በቀየረችው ኳስ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሲያደርጉ ከአንድ ደቂቃ በኃላም ካሰች ፍሰሀ ያሻገረችላትን አሁንም ነፃነት መና በግንባር በመግጨት አስቆጥራ የመጀመርያው አጋማሽ በሀዋሳ 3-0 መሪነት ተገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም ሀዋሳዎች ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ የተሻሉ ቢሆንም የአጨራረስ ችግሮች በጉልህ ሲታይባቸው ጊዮርጊሶች ከኳስ ንክኪ ባሻገር የግብ ዕድልን ለመፍጠር ከብዷቸው ታይተዋል። በዚህ አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ በግራ መስመር ተጫዋቿ ርብቃ ጣሰው መከራን አድርገው የግቡ ቋሚ የመለሰባት እና ነፃነት መና ሐት-ትሪክ መስራት የምትችልባቸውን ሁለት ዕድሎች መጠቀም ያልቻለችበት ይጠቀሳሉ። ደደቢትን ለቃ የቀድሞ ክለቧን የተቀላቀለችው ነህምያ አበራ ተቀይራ ከገባች በኃላ የሀዋሳ የማጥቃት ኃይል እንዲጨምር አስተዋፅኦ ያበረከተች ሲሆን እሙሽ ዳንኤል የሰጠቻትን ኳስ በቄንጠኛ መልኩ መትታ ለጥቂት የወጣባት ሙከራም የሚጠቀስላት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ ተቀይራ የገባችው እና ከሀዋሳ ሲ ቡድን የተገኘችው ተጫዋች ዓይናለም ዓለማየሁ ከቅጣት ምት ካደረገችው ሙከራ ውጪ ተጨማሪ አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሶስት ግቦች በሀዋሳ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህርዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት ከአርባምንጭ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በውጤቱም ሁለቱም ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጠው ለመቀጠል ተገደዋል።

*አዲስ አበባ ላይ የተደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች ሪፖርት ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን።