ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በጉጉት የሚጠበቀው የነገው ሸገር ደርቢ የዛሬው የመጨረሻ የቅድመ ጨዋታ ደሰሳችን ትኩረት ይሆናል።

የአዲስ አበባ ስታድየም ነገ 10፡00 ላይ የመዲናዋን ሁለት ታላላቅ ክለቦች የሚያገናኝበት ጨዋታ ይካሄዳል። የዘንድሮው የሊግ አጀማመሩ የተቀቃቀዘ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማው ሽንፈት እና ከሁለት ግብ አልባ ጨዋታዎች በኋላ በተስተካካይ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን መርታት ችሏል። በተመሳሳይ መልኩ ውጤት ርቆት የሰነበተው ኢትዮጵያ ቡናም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ባገኛቸው ድሎች ወደ መጀመሪያው መልካም አጀማመሩ የተመለሰ መስሏል። ሁሌም ቢሆን ትኩረትን የሚስበው የሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ አጋማሽ ካሳኩት ድል በኋላ የሚገናኙበት እንደመሆኑም የፉክክር መጠኑ ከፍ እንደሚል ይገመታል። ከውጤት አንፃርም ሲታይ አሸናፊነት ኢትዮጵያ ቡናን በሊጉ አናት የማስቀመጥ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ከመሪዎቹ ጎራ የመቀላቀል ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ የጨዋታው ወሳኝነት ከፍ ያለ ሆኗል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው የጉዳት እና የቅጣት ዜና ከሰባተኛው ሳምንት የተለየ አይደለም። የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ጌታነህ ከበደ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና መሀሪ መና ልምምድ ቢጀምሩም ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በኢትዮጵያ ቡና በኩልም አስራት ቱንጆ እና ኃይሌ ገብረትንሳይ ከጉዳት ያልተመለሱ ሲሆን በወልዋሎው ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ ወጥቶ የነበረው ሚኪያስ መኮንን ግን እንደሚሰለፍ ይጠበቃል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲሱ አሰልጣኙ ስር እየተገበረ ያለውን የአጨዋወት መንገድ ፍሬ በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ መመልከት ችሏል። ግብ የማስቆጠር ችግሩም በዚሁ ጨዋታ ላይ ተቀርፎ ታይቷል። ፊት ላይ የኤቤል ያለው ፍጥነት እና የሳላዲን ሰይድን ልምድ ማጣመሩም ለዚህ ምክንያት የሆነ ይመስላል። በነገውም ጨዋታ በመስመር ተመላላሾቹ አብዱልከሪም መሀመድ እና ኄኖክ አዱኛ የሜዳው ቁመት እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ ከተሰለፈው አቡበከር ሳኒ ሚና ጋር የሚናበብ የማጥቃት ሂደት ከቡድኑ ይጠበቃል። በተለይም በኢትዮጵያ ቡና የኋላ መስመር እና አማካይ ክፍል መካከል እንዲሁም ከተከላካይ መስመሩ ጀርባ ክፍተት ሲኖር ከሁለቱ አጥቂዎች ጫና የሚፈጠሩ ዕድሎች ለቡድኑ ጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ይህ እንዲሆን ግን በተለይም ከአማኑኤል ዮሀንስ ጋር የሚኖረውን ፍልሚያ በበላይነት መፈፀም የግድ ይላል።

ኢትዮጵያ ቡናም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ እየተገበረ ካለው አጨዋወት ጋር እየተጣጣመ እንደመጣ የሚያመለክቱ ሁለት ጨዋታዎችን አሳልፏል። በተለይም በሁለተኛው የወልዋሎ ጨዋታ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉ ትልቁ ስኬቱ ነው። ነገር ግን አሁንም ቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን የአጨራረስ ብቃት በእጅጉ ይፈልጋል። አማካይ ክፍል ላይ ክህሎትን እና ታታሪነትን ያጣመረ ቅርፅ መያዙም ለነገው ጨዋታ በቦታው የበላይ ለመሆን የሚረዳው ቢሆንም የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ለመጠቅም ግን የግድ የመስመር ተከላካዮቹን ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑ ተጋጣሚው በቦታው ካለው ጥንካሬ አንፃር ሊቸገር የሚችልበት ዕድል ይኖራል። ከዚህ ውጪ ካሉሻ አልሀሰን ከጥልቅ ቦታዎች በመሳት እንዲሁም ሚኪያስ መኮንን በተጋጣሚ የመከላከል ዞን መግቢያ ላይ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ለቡድኑ ወሳኝነታቸው የጎላ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች ከ1991 የውድድር ዓመት ጀምሮ 38 ጊዜ የተገናኙት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና  6 ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በ14 አጋጣሚዎች ደግሞ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።

                                                                      
– 73 ግቦች በተስተናገዱባቸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ 49 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 24 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን በአራት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ሲሆን በሦስቱ ደግሞ ያለግብ ከሜዳ ወጥቷል።

– በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ የቀሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ካስመዘገቧቸው ሰባት ግቦች ውስጥ ስድስቱን በሁለተኛው አጋማሽ የተቆጠሩ ነበሩ። 

ዳኛ

– ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ይህን ተጠባቂ ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንዲመራ ተመድቧል። አርቢትሩ እስካሁን በሁለተኛው ሳምንት ወልዋሎ ከመቐለ እንዲሁም በአራተኛው ሳምንት ፋሲል ከኢትዮጵያ ቡና የተገናኙባቸውን ጨዋታዎች መርቶ በድምሩ አስር የማስጠንቀቂያ ካርዶችን አሳይቷል።


ግምታዊ አሰላለፍ


ቅዱስ ጊዮርጊስ (3-5-2)

ፓትሪክ ማታሲ

አስቻለው ታመነ – ሳልሀዲን በርጌቾ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ 

አብዱልከሪም መሐመድ – ሙሉዓለም መስፍን – ናትናኤል ዘለቀ– ኄኖክ አዱኛ

አቡበከር ሳኒ

ሳላዲን ሰዓድ – አቤል ያለው

ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ዳይመንድ)

ዋቴንጋ ኢስማ

አህመድ ረሺድ – ተመስገን ካስትሮ – ክሪዝስቶም ንታምቢ – ተካልኝ ደጀኔ

 አማኑኤል ዮሀንስ

ካሉሻ አልሀሰን  – ሳምሶን ጥላሁን

                 
ሚኪያስ መኮንን

ሱለይማን ሎክዋ  – አቡበከር ነስሩ