ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በሜዳው መከላከያን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዲስ አበባ እና ክልል ስታዲየሞች ላይ ዛሬ ሲደረጉ አዲስ አዳጊው ባህር ዳር ከተማ በሜዳው መከላከያን ገጥሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።

ባለሜዳዎቹ ባህር ዳሮች ወደ ሃዋሳ አምርተው ደቡብ ፖሊስን ካሸነፉበት ጨዋታ ስብስብ በጉዳት ምክንያት ጃኮ አራፋት እና ወሰኑ ዓሊን በዜናው ፈረደ እና ፍቃዱ ወርቁ ተክተው ሲገቡ በዲሲፕሊን ምክንያት ደግሞ ወንድሜነህ ደረጄን በኄኖክ አቻምየለህ ተክተው በሚታወቁበት 4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ተጋባዦቹ መከላከያዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ወላይታ ድቻን ከረቱበት ጨዋታ ዳዊት ማሞ እና ፍቃዱ ዓለሙን በተመስገን ገብረኪዳን እና ፍፁም ገብረማርያም ለውጠው በ4-4-2 ዳይመንድ የተጨዋች አደራደር ለጨዋታው ቀርበዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማኅበር ለመከላከያዎች ስጦታ በክለባቸው አምበል ፍቅረሚካኤል ዓለሙ አማካኝነት ያበረከቱ ሲሆን ስጦታውን የመከላከያ አምበል ሽመልስ ተገኝ ተቀብሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም አስደንጋጭ ሙከራዎች ያላስተናገደው ጨዋታው ኳስን ለመቆጣጠር በሚደረግ የመሃል ሜዳ ላይ ፍትጊያ ግን ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቷል። በ3ኛው ደቂቃ ዳንኤል ኃይሉ ከአስናቀ ሞገስ የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ጎል በመምታት የመጀመሪያ የጨዋታው ሙከራ አድርጎ በመከላከያ ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ኪዳኔ ትይዩ በመመታቷ መጨረሻውን የይድነቃቸው እቅፍ በማድረግ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ተጋባዦቹ በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት ገና በጊዜ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን የግብ ማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በመከላከያዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ምንይሉ በ18ኛው እና በ19ኛው ደቂቃም ሁለት ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን በግሉ ፈጥሮ መክኖበታል።

ኳስን በመቆጣጠር ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች ወደ ግብ በመድረስ ግን ተዳክመው የግብ ማግባት አማራጫቸውን ከርቀት በመምታት በማድረግ ተጫውተዋል። የተወሰደባቸው የመሃል ሜዳ ብልጫን ቀስ በቀስ እየተረከቡ የመጡት ባህር ዳሮች በ34ኛው ደቂቃ በሚታወቁበት በመስመር ላይ አጨዋወት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። አስናቀ ሞገስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ወርቁ በግምባሩ ገጭቶ ይድነቃቸው መረብ ላይ በማሳረፍ ክለቡን መሪ አድርጓል። እየተነቃቁ የነበሩት ባለሜዳዎቹ የጣና ሞገዶቹ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ይበልጥ ተጭነው በመጫወት ጫናዎችን ተጋጣሚያቸው ላይ ለመሰንዘር ሞክረዋል። የጦሩ ተጨዋቾች በበኩላቸው የምንይሉ እና የፍፁምን ሚና በመቀያየር ለመጫወት ቢጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅያሪ በማድረግ የጀመሩት አሰልጣኝ ሥዩም ፍፁም ገብረማርያምን አስወጥተው ፍሬው ሰለሞንን በማስገባት ከእጃቸው የወጣውን የመሃል ሜዳ የበላይነት መልሰው ለመረከብ ሞክረዋል። ይሁንና ከመልበሻ ክፍል መልስ ይበልጥ ተሻሽለው የመጡት ባህር ዳሮች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ተጭነው ተጫውተዋል። የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን (በመጀመርያ ተሰላፊነት) ዛሬ ያደረገው ዜናው ፈረደ በ54ኛው ደቂቃ ኤሊያስ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ግብ ጠባቂው አውጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላም ዜናው በግል ጥረቱ ከመስመር ወደ መሀል ሰንጥቆ በመግባት የሞከረው ኳስ ሌላ የባህር ዳርን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ የሚያስችል አጋጣሚ ቢሆንም ኳሱ የውጪውን መረብ ነክቶ ወጥቷል።

ግብ ያስቆጠረው ፍቃዱ በ68ኛው ደቂቃ በአየር ላይ የመጣውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ሊያስቆጥር ቢሞክርም ኳሱ እንደ ዜናው ሙከራ የውጪውን መረብ ነክቶ ወደ ውጪ ወቷል። እነዚህ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ያስደነገጣቸው የሚመስሉት ጦሮቹ ከ70ኛው ደቂቃ በኋላ ከሚሰነዘርባቸው ጫና ለመውጣት አጥቅተው ተጫውተዋል።
በ76ኛው ደቂቃም መከላከያዎች ለተመስገን እና ለምንይሉ ረጅም ኳስ ልከው የአቻነት ጎል ለማስቆጠር ቢሞክሩም የባህር ዳር ተከላካዮች እና ምንተስኖት ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ሳሙኤልን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ቴዎድሮስ ከዳዊት እስጢፋኖስ የተረከበውን የመዓዘን ምት በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ኳሱ የግቡ አግዳሚን ነክቶ ወደ ውጪ ወጥቷል።

አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በፍሬው አማካኝነት ወደ ጎል ሲያመሩ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። በ84ኛው ደቂቃ የእለቱ የመሃል ዳኛ አዳነ ወርቁ ፍሬው ላይ ጥፋት ተሰርቷል በማለት የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን የፍፁም ቅጣት ምቱን ምንይሉ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ አድርጓል። የአቻነት እድሉን ያገኙት መከላከያዎች ያገኙትን አንድ ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት በመጠኑ አፈግፍገው ተጫውተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀረው ባህር ዳሮች ያገኙትን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ፍቅረሚካኤል በቀጥታ መቶት ይድነቃቸው እንደምንም አውጥቶበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።