የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-1 መከላከያ

በስምንተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ባህር ዳር ከተማ መከላከያን አስተናግዶ ነጥብ ተጋርቷል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሰጡትን አስተያየት እነሆ!

“ጨዋታውን አሸንፈን መውጣት ነበረብን” የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው

ስለ ጨዋታው

” በሙሉ 90 ደቂቃው ብልጫ ነበረን። ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችንም አግኝተን አልተጠቀምንም። ከሌላ ጊዜው በተለየ ብዙ አጋጣሚዎችን በተለያዩ ተጨዋቾች ብናገኝም ነገር ግን አጋጣሚዎቹን ወደ ግብ መቀየር አልቻልንም። በአጠቃላይ ጨዋታውን አሸንፈን መውጣት ነበረብን፤ ነገር ግን አልሆነም። ቢሆንም ግን በዛሬው ጨዋታ ደስ ያለኝ ነገር በቡድኔ ውስጥ ያሉት ሁሉም ተጨዋቾች ገብተው መጫወት እንደሚችሉ ያየሁበት ነው፤ እና በዚህ ደስተኛ ነኝ። ከምንም በላይ ግን ተጋጣሚዎች ወደ ባህር ዳር ሲመጡ አቻ መውጣትን እንደ እቅድ እየያዙ መምጣታቸው እና መፈራታችን ለኔ ትልቅ ስሜት ይሰጠኛል።”

ስለ መጀመርያ አስራ አንድ ምርጫቸው

” ከውጤቱ በላይ ዛሬ ደስተኛ የሆንኩት በስብስቤ ውስጥ ያሉትን ተጨዋቾች አፈራርቄ በማጫወቴ እና ዛሬ ያስገባዋቸው አዳዲስ ተጨዋቾች ያሳዩት ብቃት ነው። ባለፈው ሳምንት ወደ ሃዋሳ ተጉዘን አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ነው የተጫወትነው። በዛ ሜዳ ላይ ደግሞ ሁለት ወሳኝ ተጨዋቾችን አጥተን በሌሎች ተክተን ገብተናል። ከኋላም በነበረው ነገር (የተከላካይ ስፍራ) ደስተኛ ነኝ። ስለዚህ ስብስባችን ጥሩ ስለሆነ እያፈራረቅን እንጫወታለን፤ ጉዳቶችን እና ጫናዎችን ለመቀነስ።”

ስላገኙት ውጤት

” እንዳልኩት በጨዋታው ብልጫ ወስደን ተንቀሳቅሰናል። ብዙ ጎሎችን ማስቆጠር እንችል ነበር፤ ነገር ግን አቻ ወጥተናል። ስለዚህ የመጣውን ውጤት በፀጋ ተቀብያለው።”


” እየተመራን ወደ ጨዋታ የምንመለሰው ነገር መልካም ነው።” የመከላከያው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

ስለ ጨዋታው

” ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። በተለይ የህዝቡ ድጋፍ እና ያለው ከባቢ በጣም ያነሳሳል። በሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ጥሩ በሆንበት ሰዓት ጎል ማስተናገዳችን የራሳችን ድክመት ቢሆንም በተሻለን አቅም ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር።”

ስለ ቡድናቸው ለውጥ

“በቡድናችን ውስጥ ያየነው ለውጥ እየተመራን የምናሸንፍበት እና ወደ ጨዋታ የምንመለስበት ነገር ነው። ባለፈው ሳምንትም ወላይታ ድቻን ስናሸንፍ እየተመራን ነው ወደ ጨዋታው የተመለስነው። መመራታችን ድክመት ቢሆንም ወደ ጨዋታ የምንመለሰው ነገር መልካም ነገር ነው።”

ስለ ተጋጣሚ ቡድን

” ባህር ዳሮች ጥሩ ነበሩ። ነገር ግን የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም የጎሉ አልነበሩም። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ተሽለው ታይተዋል። ሚዛናዊ የመሆኑ ጉዳይ ግን የሚሻሻል ነገር ነው ብዬ ስለማስብ ጥሩ ነገር አይቼባቸዋለው።”

እየተመሩ አጥቂ ስለቀነሱበት ጉዳይ

” መጀመሪያ አስበን የነበረው ተመስገን ወደ መሃል እየመጣ ነገር ግን እንደ ተደራቢ አጥቂነት እንዲጫወት ነበር። በኋላ ግን ቅያሪዎች አድርገን ወደ ትክክለኛው ቦታ መልሰነው ለመጫመት ሞክረናል።”

ስለ ውጤቱ

” በጨዋታው ቀድመን ጎል አስቆጥረን ቢሆን ኖሮ ከዚህም በላይ የተሻለ ውጤት ሊያጋጥመን ይችል ነበር። ነገር ግን ከሜዳችን ውጪ እንደመጫወታችን ውጤቱ የሚያስከፋን አይደለም።”