ሪፖርት | ስሑል ሽረ ከመቐለ 70 እንደርታ ነጥብ ተጋርተዋል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ሽረ ላይ ስሑል ሽረን ከመቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ሽረም አሁንም ሙሉ ሶስት ነጥብ በሜዳው ማሳካት ሳይችል ቀርቷል።

ጨዋታው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የስሑል ሽረ ቡድን አመራሮች ለመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች የሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ምስል የያዘ ፎቶግራፍ በስጦታ ሲያበረክቱ መቐለዎችም ለስሑል ሽረ ስጦታ በማበርከት ነበር ጅማሮውን ያደረጉት። ፌድራል ዳኛ ባህሩ ተካ በሚገባ ተቆጣጥረው ባጫወቱት ጨዋታ ልክ እንደተጀመረ የመቐለ 70 እንደርታ ተጫዋቾች በፍጥነት ወደ ስሑል ሽረ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ጋብርኤል አህመድ ከሚካኤል ደስታ የተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ መሬት ለመሬት አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ኳስዋ ኢላማዋን ሳጠብቅ ወደ ውጭ ልትወጣ ችላለች። ይህም የመቐለ 70 እንደርታ የመጀመርያ የግብ ሙከራ ነበር ። 

በኳስ ቁጥጥር መቐለ 70 እንደርታወች ተሽለው በታዩበት የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ፈጣን የማጥቃት ኃይልን በባለሜዳው ላይ ያሳዩበት ነበር። በአንፃሩ በስሑል ሽረ በኩል በ19ኛው ደቂቃ ላይ አብዱሰላም አማን በቀኝ መስመር በኩል ቀጥታ ወደ ግብ የመታው እና በግብ ጠባቂው ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት ኳስ የስሑል ሽረ የመጀመርያ የግብ ሙከራ ነበር። ቶሎ ቶሎ ወደ ስሑል ሽረ የግብ ክልል የደረሱት የመቐለ 70 እንደርታ ተጫዋቾች ከግቡ በቅርብ ርቀት የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በአሚን ነስሩ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት አማኑኤል ገብረሚካኤል በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም በግብ ጠባቂው ሃፍቶም ቢሰጠኝ ድንቅ ብቃት ኳስዋ ልትድን ችላለች። በ31ኛው ደቂቃ አማኑኤል  ሁለት የስሑል ሽረ ተከላካዮችን በጥሩ ሁኔታ በማለፍ ከግብ ጠባቂው ሀብቶም ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ወደ ግብ ሳመታ ሐፍቶም ያዳነበትት ሙከራም ሌላው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር። 

በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አማኑኤል በ33ኛው ደቂቃ ላይ ከስሑል ሽረ ተከላካዮች መሀል ለመሀል ሾልኮ በመውጣት በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታም በጨዋታው በጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ሃፍቶም ቢሰጠኝ ሊያድንበት ችሏል።  የስሑል ሽረ ተጫዋቾች አብዛኛውን ክፍለ ግዜ የመቐለ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን ከማምከን ውጪ  በጨዋታው የተበለጠበት አጋጣሚ ነበር። በ37ኛው ደቂቃ ላይ የመቀለ ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ልደቱ ለማ ንፁህ የማግባት እድል ቢያገኝም ተረጋግቶ ባለመምታቱ ኳስዋ ወደ ውጭ የወጣችውም ከመጀመርያ ሙከራቸው በኋላ የምትጠቀስ ብቸኛ አጋጣሚ ነበረች። 

ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ የተቀዛቀዘ የመሰለው እና የመቐለ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተስተዋለበት ሁለተኛው አጋማሽ  በመጠኑም ቢሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ የስሑል ሽረ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታው በመመለስ ወደ መቐለ ከተማ ግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉበት ቢሆንም ከእንቅስቃሴ በዘለለ ይህ ነው የሚባል የግብ  ሙከራ ሳይስተናገድበት ያለምንም ግብ ባዶ ለባዶ ተጠናቋል። 

ስሁል ሽረዎች ከአቻ ውጤት ውጭ አሁንም ሙሉ ሶስት ነጥብ በሜዳቸው ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን አሰልጣኙም በፀጥታ ኃይል ታጅበው ከሜዳ ለመውጣት ተገደዋል፡፡

ስለ ጨዋታው የመቐለ ከተማው አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ለቃለ መጠይቅ ፍቃደኛ ባይሆኑም የስሑል ሽረን አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሀዬን ሀሳብ ግን አካተናል፡፡
” ጨዋታው በጣም ከባድ ነበር። ቋሚ ተሰላፊዎቻችን ወደ አምስት የሚጠጉት በጉዳት ምክንያት መጠቀም አልቻልንም። በዚህም ምክንያት በውጤታችን ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሮብናል። በተከላካይ ቦታ ዛሬ ሁለት ከተስፋ ቡድን ያደጉ ልጆችን ነው የተጠቀምነው፤ ቡድናችን በተጫዋች ጉዳት ሳስቷል። ይህን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ በቀጣይ ጠንካራ ስራ መስራት አለብን። በሜዳችን ማሸነፍ ካልቻልን አሳሳቢ ነው። ከጉዳት የሚነሱ ስላሉ ይህን ችግራችንን ደግሞ እንደምንቀርፍ እርግጠኛ ኝ።