ከፍተኛ ሊግ | በምድብ ለ የአምሰተኛ ሳምንት ቀሪ አንድ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ አሸንፏል

ባሳለፍነው ሳምንት ታህሳስ 19 የወልቂጤ አምበል የነበረው መዝገቡ ወልዴ ከዚህ ዓለም በመለየቱ ምክንያት ትላንት ሊደረግ የነበረውና ወደ ዛሬ የተሸጋገረው የወልቂጤ ከተማ እና ኢኮስኮ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ ተከናውኖ በባለሜደው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 
የመዝገቡ ወልዴ ስርአተ ቀብር ቅዳሜ ታህሳስ 20 ሲፈፀም እንግዳው ቡድን ኢኮስኮ ጭምር በቦታው በመገኘት ቤተሰቡን እንዲሁም የወልቂጤን ደጋፊ በማፅናናት የእግር ኳስ ቤተስብነታቸውን አሳይተዋል። ይጀመራል ከተባለበት ሰዓት በመጠኑ ዘግይቶ የተጀመረው ጨዋታው የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን በርካታ ደጋፊዎችም ጥቁር ልብስ በመልበስ የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል። ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ በ2ኛው ደቂቃ ላይም ለመዝገቡ ወልዴ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ለአንድ ደቂቃ ያህል ጭብጨባ ተደርጓል። (ተጫዋቹ ይለብሰው የነበረው ሁለት ቁጥር ማልያ በክለቡ ለሁለት ዓመታት እንዳይለበስ መወሰኑ ይታወሳል።)

ጨታው መሐመድ ሁሴን በ15 ኛው እና በ20ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠራቸው ጎሎች ወልቂጤ ከተማ 2-0 ሲያሸንፍ በውጤቱም ደረጃውን ወደ አራተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል። 

ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስታያየታቸውን በዚህ መልኩ ሰጥተውናል።

አሰልጣኝ ደረጀ በላይ – ወልቂጤ ከተማ 

ከጨዋታው በፊት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎል ማስቆጠር እንዳለብን ከተጫዋቾቼ ጋር አውርተናል። ለዛም የሚሆን አጨዋወት ይዘን ገብተናል። ባሰብነው መንገድ ጎሎችን አስቆጥረናል። ከግቡ መቆጠር ባኋላ ወደ ኋላ እየተሳብን ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረናል። በሁለተኛው አጋማሽ በመጨረሻው ደቂቃ ላይም እንደመጀመሪያው በማድረግ ተጭነን መጫወት ችለናል።

ተጋጣሚያችን ጠንካራ ቡድን ነው። ስብስቡም እንደዛው። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎል ባናስቆጥርበት እየቆየ ሊከብደን ይችል ነበር። ኳስ መስርተው ለመጫወት ይሞክሩ ነበር።

ስለ ዳኝነቱ መናገር ባልፈልግም በሁለተኛው አጋማሽ ላይ አህመድ ሁሴን ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጎትቶ ወድቆ ነበር። ፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር። ለኛ የሶስተኛ የጎል እድል ነበር። ቀሪው ነገር ግን ጥሩ ነበር።

በስተመጨረሻ ይህን ድል በጣም እንፈልገው ነበር። መዝገቡ የሚልብሰው 2 ቁጥር፤ የገባው ጎል ሁለት ጎል ነው። የጨዋታውም ድል ለወልቂጤ ህዝብ ደስታን እንደሚፈጥር እርግጠኛ ነኝ። ደጋፊው የነበረው አደጋገፍ በጣም ልዩ ነበር። ውጤቱ ይገባዋል።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ኢኮስኮ

የጨዋታው ውጤት የነበረውን እንቅስቃሴ አይገልፀውም። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተገኙ ሁለት ግቦች ነው ጨዋታው ያለቀው:: ተጫዋቾቼ በመጀመሪያው 20 ደቂቃ ላይ ተደናግጠው ነበር። የህዝቡ ድጋፍ ግን ልዩ ነበር። የተጫዋች መዝገቡ ሀዘን ትልቅ ቁጭት ነበር የፈጠረባቸው። በዚህ ድጋፍ ውስጥ ነው ጎል የገባው። የመጀመሪያው ጎል ግብ ጠባቂያችን ቀድሞ ወጥቶ ማዳን ይችል ነበር፤ ሁለተኛውም የራሳችን ስህተት ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገባን ሲሆን በርካታ ሙከራዎች ማድረግ ችለናል። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ተጭነን ብንጫወትም ያገኘነውን የግብ አጋጣሚ መጠቀም አልቻልንም ነበር። ስለ ዳኝነቱም እንዲ ነው እንዲያ ነው ማለት አልፈልግም። ጎሎችም የተቁጠሩብን በራሳችን ስህተት ነው።

በአጠቃላይ ወልቂጤ ክለብ እና የስፖርት ቤተሰቡን  ፈጣሪ ያጽናቹ ነው የምንለው በኢኮስኮ ስም።