ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሦስት የውጭ ተጫዋቾቹ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

በክረምቱ የዝግጅት ወቅት በተሰናባቹ አሰልጣኝ ማኑኤል ቫስ ፒንቶ የሙከራ እድል ተሰጥቷቸው በክለቡ ከፈረሙት አምስት የውጭ ተጫዋቾች መካከል አዲሱ እንግሊዛዊ አሰልጣኝ ስትዋርት ሀል በሶስቱ የውጭ ተጫዋቾች ብቃት ደስተኛ ባለመሆናቸው ለአሌክስ ኦሮትማል እና ኢሱፍ ቡርሀና እና ካሲሙ ታይተስ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ታውቋል።

በክረምቱ የኬኒያው ሊዮፓርድስን ለቆ ፈረሰኞቹን ተቀላቅሎ የነበረው ናይጄርያዊው አጥቂ አሌክስ ኦሮትማል በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ባሳየው ደካማ ብቃት የክለቡ ደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያሰሙበት መታየቱ የሚታወስ ነው። ሌላው በፈረሰኞቹ የመጨረሻ መስጠንቀቂያ የደረሰው ቶጎዊው የመስመር ተከላካይ ኢሲፉ ቡርሐናን ክለቡ ካደረጋቸው ሰባት የሊግ ጨዋታዎች በአምስቱ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ከመቀመጥ በዘለለ አሰልጣኙን አሳምኖ በአንድም ጨዋታ ላይ የመጀመርያ ተሰላፊ መሆን አልቻለም። ጋናዊው አማካይ ካሲሙ ታይሰንም አንድ ጨዋታ ብቻ በመጀመርያ ተሰላፊነት ከመጀመሩ በቀር አመዛኙን ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ አሳልፏል። የቡድን መሪው አቶ ታፈሰ በፃፉት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤም ካሱሙ ከዚህ ቀደም ክለቡ ባዘጋጀው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ያለ ትጥቅ ወደ ሜዳ መምጣቱን እና ቡድኑ ካደረጋቸው ጨዋታዎች አንፃር እጅግ ዝቅተኛ አገልግሎት መስጠቱን በመግለፅ በቶሎ ብቃቱን አሻሽሎ የሚፈለገውን አገልግሎት ካልሰጠ እንደማይታገሱ ገለፀዋል።

ሶስቱ ተጫዋቾች ምናልባትም በሁለተኛው ዙር በአሰልጣኝ ስቴዋርት ስር ላይቀጥሉ እንደሚችሉ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል። በተያያዘም ዛሬ ክለቡ አንድ ናይጄሪያው አጥቂ አስመጥቶ ሙከራ እያደረገ ሲሆን በቅርብ ቀናት ውስጥ ተጨማሪ ሦስት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው በማስመጣት የሙከራ ጊዜ እንደሚሰጥ መሰማቱ የተጫዋቾቹን ቆይታ አጠራጣሪ አድርጎታል።