የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በዩጋንዳ ይደረጋል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግርኳስ ማህበር ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫን ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በዩጋንዳ አዘጋጅነት እንደሚያካሂድ ይፋ አድርጓል።

እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም በታንዛኒያ አዘጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በ2010 ዓ.ም በኤርትራ ከተሰናዳ በኋላ ላለፋት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቆይቷል። የሴካፋ አመራር በወጣቶች እግርኳስ ላይ በይበልጥ ለመስራት ባደረገው ስምምነት ውድድሩ ከ8 ዓመታት በኋላ ሲመለስ የአዘጋጅነት ዕድሉን ያለፉት ሁለት ውድድሮች ሻምፒዮን የነበረችው ዩጋንዳ አግኝታለች።

በውድድሩ 11 የሴካፋ አባል ሃገራት – ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ እና ሶማሊያ – እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ የሰጡ ሲሆን ዛንዚባር እንደማትሳተፍ ያሳወቀች ብቸኛዋ አባል ሃገር ሆናለች። ዛንዚባር በውድድሩ የማትሳተፈው የእግርኳስ ፌዴሬሽኗን በአዲስ መልክ የማዋቀር ሂደት ላይ ስለሆነች መሆኑንም የሴካፋ ዋና ፀሐፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ አስታውቀዋል።

በዩጋንዳ ጉሉ እና ጂንጃ በተሰኙ ከተሞች ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ውድድር ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማህበር 50,000 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አድርጓል። ከጥር 6 እስከ 19 ድረስ እንዲካሄድ መርሃግብር ወጥቶለት የነበረው ውድድር ግን ሊራዘም እንደሚችል ዋና ፀሐፊው ፍንጭ ሰጥተዋል።

“ዩጋንዳ ውድድሩን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ላይ የምትገኝ ስለማይመስል የዩጋንዳ ፌዴሬሽን ተለዋጭ ቀናት እንዲሰጠን ጠይቀናል፤” ሲሉ ኒኮላስ ሙሶንዬ ተናግረዋል።

በውድድሩ የሚሳተፉ ሃገራት ባመዛኙ ዝግጅት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ውድድሩ የሚጀመርበት ትክክለኛ ቀን አለመታወቁ ግን እንደ ኬንያ ያሉ ሃገራት የካምፕ ዝግጅታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያራዝሙ አስገድዷል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሴካፋ ውድድር በተጨማሪ በየካቲት ወር በአስመራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው እና በኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ ወጣት ቡድኖች መሃከል በሚደረገው ‘የሰላም እና ወዳጅነት ዋንጫ’ ላይ እንደሚሳተፍ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *