የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ ዋና ጸኃፊ ሾመ

ላለፉት ሁለት ዓመታት ቋሚ ዋና ጸኃፊ ያልነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዲስ ዋና ጸኃፊ መቅጠሩን አስታውቋል፡፡

ልክ የዛሬ ዓመት መስከረም ታደሰን በመተካት አቶ ሰለሞን ገ/ሥላሴ የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ጸኃፊ ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ባደረገው ስብሰባ በቅርቡ በተሰራው የአደረጃጀት ሪፎርም ጥናት መሠረት የሰው ሐብት አደረጃጀት ምደባ በአዲስ መልክ እንዲከናወን ውሳኔ በማሳለፍ ኢያሱ መርሐ-ፅድቅ (ዶ/ር) በቋሚነት ዋና ጸኃፊ አድርጎ መምረጡን አስታውቋል።

ዶ/ር ኢያሱ በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩ ሲሆን ሶስተኛ (ዶክትሬት) ዲግሪያቸውን ደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንዳገኙ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ ቀደምም በ1990ዎቹ አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር) ፌዴሬሽኑን በሚመሩበት ወቅት ለአጭር ጊዜ ማገልገላቸውም ታውቋል። 

ያለፉትን 12 ወራት በጊዜያዊ ዋና ጸኃፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ በምክትል ዋና ጸኃነት የተመደቡ ሲሆን የእግርኳስ ልማት ኃላፊነትን ደርበው እንደሚሰሩም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። 

ባለፉት አምስት ዓመታት ያልተረጋጋ ቦታ በሆነው የፌዴሬሽኑ ዋና ጸኃፊነት በ2005 አቶ አሸናፊ እጅጉ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ በቢጫ ካርድ መረሳት ምክንያት መቀጣቷን ተከትሎ ከቦታው ተነስተው በምትካቸው አቶ ይግዛው ብዙዓየሁ ተሹመዋል። አቶ ይግዛውም ለወራት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 2006 ላይ በምትካቸው ተሿሚ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝም በ2007 መጨረሻ ኢትዮጵያ በሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ድልድል ውስጥ ሳትገባ መቅረቷን ተከትሎ በጊዜያዊነት በአቶ ወንድምኩን አላዩ ተተክተዋል። በ2010 መጀመርያ አቶ ወንድምኩን ራሳቸውን ከስራው በማግለላቸው ወ/ሪት መስከረም ታደሰ ለአጭር ወራት ከመራችው በኋላ አቶ ሰለሞን ለአንድ ዓመት በጊዜያዊነት ቦታውን ይዘው ቆይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *