ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ አዳማ ከተማ

ከ9ኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብሮች አዲስ አበባ ላይ መከላከያ አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል። 

በሊጉ በዕኩል ስምንት ነጥቦች በ9 እና 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መከላከያ እና አዳማ ከተማ ነገ 11፡00 ላይ በሚጀምረው የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብራቸው እርስ በርስ ይገናኛሉ። ከሜዳቸው ውጪ ጥሩ ነጥብ እየሰበሰቡ የሚገኙት መከላከያዎች ከባህር ዳር ጉዟቸውም ከአንድ ነጥብ ጋር ነው የተነለሱት። ሦስት ተስተካካይ ጨዋታዎች እጃቸው ላይ እንደመኖሩም ሊጉን መምራት ከመቻል ጀምሮ ጠንካራ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆነው እስከመዝለቅ የሚያስችላቸው ዕድል አሁንም እጃቸው ላይ ይገኛል። እንግዶቹ አዳማዎች ደግሞ ከድል መልስ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበት ይህ ጨዋታ አካሄዳቸውን ለማስተካከል ዕድል የሚያገኙበት ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት መቐለን ረተው ወደ መዲናዋ ሲመጡ በቡና ሽንፈት ማስተናገዳቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ደቡብ ፖሊስን ከረቱ በኋላ መከላከያን ለመግጠም ተዘጋጅተዋል። ወጣ ገባ የሆነውን አቋማቸውን ለማሳመርም ሦስት ነጥቡ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል። 

መከላከያ አዲስ ጉዳት ያስተናገደም ሆነ ቅጣት የተጣለበት ተጫዋች የሌለው ሲሆን አቅሌሲያስ ግርማ ፣ አማኑኤል ተሾመ እና አቤል ማሞ ግን አሁንም ከጉዳታቸው አላገገሙም። በአንፃሩ አዳማ ከተማ ነገ ከጉዳት መልስ የወሳኙን አማካይ ከነዓን ማርክነህን ግልጋሎት የሚያገኝ ሲሆን ምኞት ደበበም  ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ እንዳገገመ ታውቋል። ከዚህ ውጪ ግን ዓመለ ሚልኪያስ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ሱራፌል ጌታቸው በጉዳት አጥቂው ሙሉቀን  ታሪኩ ደግሞ በሆድ ህመም ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል።

ከጉዳት እና ቅጣት መልስ ተጫዋቾቹን ያገኘው መከላከያ አማራጮቹ የሰፉለት ይመስላል። ነገ አዳማን ሲገጥምም ጠንካራ ጎኑ ከሆነው የአማካይ ክፍሉ ተከላካይ ሰንጣቂ የሆኑ የመጨረሻ ኳሶችንም ሆነ ቀጥተኛ የአየር ላይ ኳሶችን ወደ ፊት ለማሳለፍ የሚያስችሉት አማራጮች ይኖሩታል። ነገር ግን በተለይም ከተመስገን መመለስ በኋላ ይበልጥ ጉልበት ኖሮት በሚታየው መሀል ለመሀል ወደሚሰነዝረው ጥቃት እንደሚያደላ ይጠበቃል። በዚህ አካሄድ ቡድኑ የሜዳውን ስፋት ለማግኘት የመስመር ተከላካዮቹን የመጠቀም ግዴታው እንዳለ ሆኖ ሁለቱን አጥቂዎች ለማግኘት ግን ከኢስማኤል ሳንጋሪ እና አዲስ ህንፃ ጥምረት ጋር ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል። 

የከንዓን አለመኖን ተከትሎ በደቡብ ፖሊሱ ጨዋታ ወደ 4-4-2 መጥተው የነበሩት አዳማዎች ነገ ዳዋ ሁቴሳን በብቸኛ አጥቂነት ወደ መጠቀሙ እንደሚመለሱ ይገመታል። ከተጋጣሚያቸው የማይተናነስ የአማካይ ክፍል የስብስብ ጥራት ያላቸው አዳማዎች  የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት በሚኖረው ፉክክር በቀላሉ የሚቀመሱ አይመስሉም። የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ የሆነው ከንዓንን እንቅስቃሴ ተከትሎም በተጫዋቹ ግራ እና ቀኝ በሚኖሩት የማጥቃት አማካዮች በኩል ለዳዋ ሁቴሳ የመጨረሻ ኳሶችን በማድረስ ከግቡ ርቆ ስከላከል የሚቸገረው የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ መስመር መፈተናቸው የሚቀር አይደለም። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡደኖች በአጠቃላይ በሊጉ 25 ጊዜ ተገናኝተው 7 እኩል ጊዜ ሲሸናነፉ በ11 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡ በእነዚህ ግንኙነቶች መከላከያ 18 ግቦች ሲያስቆጥር አዳማ 17 አስቆጥሯል፡፡

– አዲስ አበባ ላይ 12 ጊዜ ተገናኝተው መከላከያ በአራቱ ድል ሲቀናው አዳማ በሁለቱ አሸንፏል፡፡ ስድስት የአዲስ አበባ ግንኙነታቸው በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው፡፡

– እስካሁን አዲስ አበባ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገው መከላከያ አንዱን አሸንፎ በሌላኛው ድል ቀንቶታል።

– አዳማ ዘንድሮም ከሜዳው ውጪ ባለው ደካማ አቋሙ ሲቀጥል ከሦስት ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ነው።

ዳኛ

– ምንም ካርድ ያልታየበትን የአምስተኛ ሳምንቱን የድሬዳዋ ከተማ እና ደደቢት ጨዋታ ከቅጣት መልስ የዳኛው ፌደራል ዳኛ ኄኖክ አክሊሉ ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ 

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ

ተመስገን ገብረኪዳን

ፍፁም ገብረማርያም – ምንይሉ ወንድሙ      

አዳማ ከተማ (4-2-3-1)

ሮበርት ኦዶንካራ

ሱለይማን ሰሚድ  – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ

አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ 

ቡልቻ ሹራ – ከነዓን ማርክነህ – በረከት ደስታ

ዳዋ ሁቴሳ  

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *