ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ወላይታ ድቻ

ነገ የሚከናወነውን የደደቢት እና ወላይታ ድቻ የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በስምንተኛው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረውን ጨዋታ ሳያደርግ የቀረው ደደቢት ነገ ወላይታ ድቻን በትግራይ ስታድየም 09፡00 ላይ ያስተናግዳል። እስካሁን የነጥብ እና የግብ መንገዱን ማግኘት የተሳናቸው ደደቢቶች በመጨረሻው ጨዋታቸው እዛው መቐለ ላይ በወልዋሎ ዓ/ዩ 1-0 መረታታቸው የሚታወስ ነው። ከሰባት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥቦችን ይዘው በሊጉ አጋማሽ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ሳምንት ድሬዳዋን ሶዶ ላይ ገጥመው ነጥብ ተጋርተዋል። ድቻዎች በሜዳቸው ካገኟቸው ጠባብ ድሎች ውጪ የእስካሁኑ ጉዟቸው ወጣ ገባ የሚል ዓይነት ሆኗል። የነገው ጨዋታ ያለአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ለደደቢት የመጀመሪያ የሊጉ ለወላይታ ድቻ ደግሞ የመጀመሪያው የሜዳ ውጪ ድል ሆኖ የመመዝገብ ዕድል ይኖረዋል።

ደደቢት ለነገው ጨዋታ በሙሉ ስብስቡ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ ሆኖ የሚቀርብ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩልም እርቅይሁን ተስፋዬ እና ኃይማኖት ወርቁ ብቻ በጉዳት ጨዋታው እንደሚያልፋቸው ታውቋል።

በወልዋሎው ጨዋታ የአቀራረብ ለውጥ የታየበት ደደቢት የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ለማግኘት ከሚያደርገው ጥረት በመቆጠብ ጥንቃቄን ሲመርጥ ተስተውሏል። ቡድኑ በነገውም ጨዋታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን የግራ እና ቀኝ አማካዮቹን ወደ ኋላ በመሳብ መከላከሉን እንዲያግዙ በማድረግ የተጋጣሚያቸውን የመስመር ጥቃት ለመመከት እንደሚንቀሳቀሱ ይጠበቃል። ወደ ብቸኛ አጥቂያቸው የሚያደርሷቸው ቀጥተኛ ኳሶችም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት አማራጮች የሚሆኑ ይመስላል። በመሆኑም በወጣቶቹ የመስመር አማካዮቻቸው ማጥቃትን ምርጫቸው የሚያደርጉት ድቻዎች ክፍተቶችን ለመፍጠር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ድቻዎች በነዓብዱልሰመድ ዓሊ ኳስ አቀጣጣይነት መሀል ለመሀል ጫና በመፍጠር ከፊት አጥቂያቸው ጋር የመገናኘት አካሄዳቸውም ቀላል ላይሆን ይችላል። የሁለቱ ቡድኖች የእስካሀኑ ደካማ ግብ የማስቆጠር ሂደት ሲታይ ግን ጨዋታው በበርካታ ግቦች የታጀበ ላይሆን እንደሚችል ይገመታል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ቡድኖቹ በብዛት በመሸናነፍ የጨረሷቸውን አስር የሊግ ግንኙነቶች አድርገዋል። ከነዚህ ውስጥ አምና አዲስ አበባ ላይ ያደረጉት ጨዋታ ብቻ ያለግብ ሲጠናቀቅ ደደቢት አምስት ጊዜ ወላይታ ድቻ ደግሞ አራት ጊዜ ባለድል ሆነዋል።

– በጨዋታዎቹ ደደቢት 17 ወላይታ ድቻ ደግሞ 12 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

– ደደቢት እስካሁን ያደረጋቸውን ጨዋታዎች በሙሉ ሲሸነፍ ስምንት ግቦችን አስተናግዶ አንድም ግብ አላስቆጠረም።

– ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲሸነፍ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ መጋራት ችሏል።

ዳኛ

– በሦስተኛው ሣምንት ሲዳማ ቡና ከባህር ዳር ከተማ በስድተኛው ሳምንት ደግሞ ፋሲል ከነማ ከመከላከያ ያደረጓቸው ጨዋታዎችን ዳኝቶ አስራ ሰባት የማስጠንቀቂያ ካርዶች የመዘዘው እና ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶች የሰጠው ፌደራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ይህን ጨዋታ ይመራዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

መድሀኔ ብርሀኔ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ

አብርሀም ታምራት – የአብስራ ተስፋዬ

እንዳለ ከበደ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ

አኩዌር ቻሞ

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ኄኖክ ኢሳያስ – እዮብ ዓለማየሁ

ባዬ ገዛኸኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *