ከፍተኛ ሊግ ሀ | ለገጣፎ የመጀመርያ ሽንፈቱን ሲያስመዘግብ ኤሌክትሪክ እና ሰበታ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስድስተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች ተደርገው ወሎ ኮምቦልቻ፣ ሰበታ ከተማ፣ አክሱም ከተማ፣ አውስኮድ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸንፈዋል።

ፌዴራል ፖሊስ 0-0 ቡራዩ ከተማ

(በዮናታን ሙሉጌታ)

ኦሜድላ ሜዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ እንቅስቃሴ ረጃጅም ኳሶች የተበራከቱበት እና ብዙ የግብ ሙከራዎችም ያልተደረጉበት ነበር። ባለሜዳዎቹ ፌደራል ፖሊሶች የተሻለ አጫጭር ቅብብሎችን ለመተግበር ቢሞክሩም የፈለጉትን ያህል ተፅእኖ ፈጥረው ወደ ግብ መድረስ አልቻሉም። ለፊት ወጥቂው ሰይፈ ዘክር የሚልኳቸው ቀጥተኛ ኳሶችም ቢሆኑ ለቡራዩ ተከላካዮች የተመቹ ነበሩ። 38ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ተካ ያነሳውን የማዕዘን ምት ሰይፉ መገርሳ በግንባሩ ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት ሙከራ የቡድኑ የተሻለ የግብ አጋጣሚ ነበር።  15ኛው ደቂቃ ላይ ሙጃይድ መሀመድ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን የጣለው ቅጣት ምት በፌደራል ተጫዋቾች ተጨርፎ ሊገባ ሲል በግቡ አግዳሚ የተመለሰባቸው ቡራዩዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው አጋማሽ ገፍተው መጫወት ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ግን አልሆነላቸውም። አጥቂው አብዱልከሪምን መዳረሻ የሚያደርጉት ረጃጅም ኳሶቻቸው እና ከቆሙ ኳሶች ለመፍጠር የሞከሯቸው የግብ አጋጣምዎችም ፍሬ ሳያፈሩ ጨዋታው ወደ እረፍት አምርቷል።

ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴም ከመጀመሪያው በብዙ መልኩ ያልተለየ ነበር። ሲጀመር ወደ ግራ መስመር አድልተው ለማጥቃት ይሞክሩ የነበሩት ቡራዩዎች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ላይ ተመስርተው አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት ቀጥለዋል።  ሆኖም ጨዋታው በገፋ ቁጥር ከሙከራ ርቀው የቆዩ ሲሆን 55ኛው ደቂቃ ላይ  ከግራ መስመር ያሻገሩትን ኳስ ኤልያስ መንግስቱ በግንባሩ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የቡድኑ የተሻለ ሙከራ ነበር። ነገር ግን በመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የፌደራሎችን የማጥቃት ፍላጎት ተከትሎ በነበረው ክፍተት ቡድኑ ያገኛቸው ንፁህ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ተቀይረው በገቡት  ዘሪሁን ታምሩ እና ጫላ ከበደ ደካማ ሙከራዎች መክነው ቀርተዋል።  

ፌደራል ፖሊሶች በበኩላቸው በተቻላቸው መጠን ኳስ ለመያዝ ሲጥሩ ቢስተዋሉም በአመዘኙ ወደ ግብ የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ግን ከቆሙ ኳሶች የመነጩ ነበሩ። በተለይም ከረጅም ርቀት ያገኟቸው የቅጣት ምቶችን ወደ ግብ ሙከራነት በተደጋጋሚ ለመለወጥ ቢጥሩም የቡራዩው ግብ ጠባቂ አሸብር ደምሴ ጥረት ታክሎበት ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይም የመስመር አማካዩ አዳነ ተካ ከግራ መስመር በመግባት አክርሮ የሞከረው የ75ኛ ደቂቃ ሙከራ ለግብ የቀረበ ቢሆንም በአሸብር ተመልሷል። አሸብር ከ አራት ደቂቃዎች በኋላ የፌደራሉ ረጅም  አማካይ አብነት ደምሴ በግንባሩ የሞከረበትን ሌላ ጠንካራ ኳስም ማውጣት ችሏል። 

ጨዋታው 0 0 ከመጠናቀቁ ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ በፌደራል ፖሊስ አጋማሽ የግራ መስመር በኩል በቡድኑ የቀኝ መስመር ተከላካይ ዳንኤል መኮንን እና በቡራዩው ዳንኤል ለታ መካከል በተጀመረ ጉሽሚያ መጠነኛ ግርግር ተፈጥሮ ሁለቱ ተጫዋቾች የፌደራል ዳኛ ኃይሌ ኪዳኔ ቀይ ካርድ ሰለባ ሆነዋል።

አውስኮድ 2-1 ወልዲያ

(ሚካኤል ለገሰ)

ባህርዳር ስታድየም ላይ ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አውስኮዶች ከወትሮው በተለየ ጠንክረው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ተጋባዦቹ ወልድያዎች ደግሞ በመጠኑ ተዳክመው ታይተዋል። ፈጣን እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደ ፍጥነቱ ብዙ የጎል ሙከራዎች አላስተናገደም። ጨዋታው ለግብ የቀረበ ሙከራ ያስተናገደው በ19ኛው ደቂቃ ሲሆን ሙከራውን ያደረገው የአውስኮዱ ኤርሚያስ ኃይሌ ነበረ። ኤርሚያስ በግል ጥረቱ ወደ ወልድያ ሳጥን ገብቶ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ከፍያለው ሃይሉ አድኖበታል። ኳስን አደራጅተው ለመጫወት የሚሞክሩት ወልድያዎች የሚያገኙዋቸውን ኳሶች በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ለነበረው ተስፋዬ ነጋሽ በማድረስ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ከመስመር እየተነሳ ወደ መሃል በመግባት ሲጫወት የነበረው ተስፋዬ የአውስኮድ የተከላላይ ክፍል በመረበሽ እድሎችን ለመፍጠር ሞክሯል። በ35ኛው ደቂቃም ተስፋዬ ከእንድሪስ ሰዒድ ያገኘውን ያለቀለት ኳስ ቺፕ አድርጎ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም ወልድያዎች በእንድሪስ ሰኢድ አማካኝነት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚ ፈጥረው መክኖባቸዋል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ለመነቃቃት የሞከሩት አውስኮዶች የአቻነት ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። 

በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎች ጥሩ የነበሩት ባለሜዳዎቹ  በ11 ደቂቃ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ቶሎ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል። ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ አውስኮዶች በቀኝ በኩል ወደ ወልድያዎች ሳጥን በመግባት ያሻገሩትን ኳስ የወልዲያው ተከላካይ ሲሳይ ሚዴቅሳ አወጣለው ብሎ ራሱ ላይ በማግባት ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል። ከ7 ደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ በቀኝ በኩል የመጡት አውስኮዶች ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቶባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ሐቁምንይሁን ገዛኸኝ ወደ ጎልነት ቀይሮት መሪ ሆነዋል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ የመሐል ሜዳውን የበላይነትን የተነጠቁት ወልዲያዎች ተጨማሪ የአማካይ ተጨዋቾችን ቢያስገቡም የበላይነቱን መልሰው መረከብ አልቻሉም። በ63ኛው ደቂቃ ወልዲያ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በእንድሪስ ሰዒድ አማካኝነት የቀረቡ ቢመስልም የአውስኮዱ ግብ ጠባቂ ደረጄ ዓለሙ አድኖባቸዋል። ሁለተኛውን ግብ ካስቆጠሩ በኋላ አውስኮዶች በተደበላለቀ የጨዋታ ዘይቤ መጫወታቸው ሲታይ አልፎ አልፎ በሚሰነዝሩት የመልሶ ማጥቃት እድሎች ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዚሁ የጨዋታ ስልት በ81ኛው እና በ87ኛው ደቂቃ በወ/አገኝ በለጠ እና በኤርሚያስ ኃይሌ አማካኝነት ወደ ግብ ቢደርሱም ኳሶቹ ኢላማቸውን በመሳታቸው መረብ ላይ ሳያርፉ ቀርተዋል። በ89ኛው ደቂቃ ወልድያ ቀይረው ወደ ሜዳ ባስገቡት ቶስላች ሳይመን አማካኝነት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው አቻ ለመሆን ቢጥሩም የአውስኮድ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውባቸዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ 2ለ1 ተጠናቋል።

ሌሎች ጨዋታዎች

ወደ ኮምቦልቻ ያመራው ለገጣፎ ለገዳዲ 1-0 ተሸንፎ የዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል። አክሱም ላይ አክሱም ደሴ ከተማን 2-1 ሲያሸንፍ ኤሌክትሪክ ገላን ከተማን አስተግዶ በአንጋፋው አጥቂ ታፈሰ ተስፋዬ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል። ሰበታ ከተማ አቃቂ ቃሊቲን 3-1 ሲያሸንፍ ኢብራሂም ከድር፣ ጫላ ድሪባ እና እንዳለ ዘውዴ የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *