ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባጅፋርን በማሸነፍ ከመሪው ያለውን ልዩነት መልሶ አጥብቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ከመመራት ተነስቶ 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ሁለቱም ክለቦች ባሳለፍነው ሳምንት እዚሁ ሀዋሳ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ከተጠቀሙበት ስብስብ መካከል የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሀዋሳዎች ተክለማርያም ሻንቆ፣ ነጋሽ ታደሰ እና አክሊሉ ተፈራን አስወጥተው ሶሆሆ ሜንሳህ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና አዳነ ግርማን ሲተኩ በጅማ አባጅፋር በኩል በተስፋዬ መላኩ (ቀይ)፣ አስቻለው ግርማ እና ኄኖክ ገምቴሳ ምትክ ያሬድ ዘውድነህ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ንጋቱ ገብረሥላሴ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ገብተዋል፡፡

ፌድራል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በጥሩ ሁኔታ በመራው ጨዋታ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ የእንቅስቃሴም ሆነ የግብ መከራዎች ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል። ጅማዎች የግብ ሙከራ በማድረጉ ቀዳሚወቹ ነበሩ፤ በአንደኛው ደቁቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት የነበረው ማማዱ ሲዴቤ ሞክሮ በሶሆሆ ሜንሳህ ከሽፎበታል። ሀዋሳዎች ምላሽ የሰጠ አጋጣሚን ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ሲፈጥሩ ዳንኤል ደርቤ አሻምቶ አዳነ ግርማ ለጥቂት ያመለጠችው አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበረች። በ6ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሀንስ ወደ ግብ ክልል የላካትን ኳስ በእለቱ በርካታ አጋጣሚዎችን እያገኘ ሲያመክን የነበረው አዳነ ግርማ አግኝቷት አዳማ ሲሶኮ ቀድሞ አስጥሎታል። 

በ12ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባጅፋሮች የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ ስህተት በግልፅ ያሳየች ግብ ማስቆጠር ችለዋል። አማካዩ ይሁን እንደሻው በግራ የሀዋሳ የግብ መስመር የተገኘችውን ቅጣተ ምት ሲያሻማ ማማዱ ሲዲቤ ወደ ግብነት ለውጧት አባጅፋሮችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ በኋላ ገና በጊዜ መከላከልን የመረጡት ጅማዎች ማማዱ ሲዴቤ በግሉ የሀዋሳን ተከላካይ ሲረብሽ እና ሲያስጨንቅ ከመታየቱ ውጭ በሀዋሳ ከተማ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። ቀጣዮቹን አስር ደቀላዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በ22ኛው ደቂቃ መስዑድ መሐመድ በጉዳት ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ሊቀጥል አልቻለም። 

25ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ክልል ውስጥ የጅማ አባጅፋሩ የመሀል ተከላካይ አዳማ ሲሶኮ እስራኤል እሸቱን በመጥለፉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን ወደ ግብነት ቀይሯት ሀዋሳን አቻ ማድረግ ችሏል። ለዚህች ፍፁም ቅጣት ምት መገኘት እስራኤልን ጠልፎ የነበረው አዳማ ሲሶኮ ወደ አራተኛ ዳኛው አምርቶ ለጠብ ሲጋበዝ ቢስተዋልም የእለቱ ዳኛ ከቃል ማስጠንቀቂያ ውጭ ምንም እርምጃ ሳይወስዱበት የቀሩበት ክስተት አስገራሚ ነበር፡፡

ሀዋሳዎች ከአቻነቱ ጎል በኋላ በሁለቱም መስመሮች የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጫና መፍጠር ችለዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል እስራኤል እሸቱ ያሻገራትን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አዳነ ግርማ አግኝቷት በቀላሉ ሲመታት ዳንኤል አጄይ ሲይዝበት 42ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ በግል ጥረቱ አመቻችቶ የሰጠው ኳስ ታፈሰ ሰለሞን እግር ስር ደርሳ ታፈሰ በቄንጠኛ ምት ወደ ግብ ሲመታት የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በ44ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከደስታ ዮሀንስ በረጅሙ የተገኘችን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን አየር ላይ እያለች በግንባር አመቻችቶለት አዳነ ግርማ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎልነት ቀይሯል። ሀዋሳም ወደ 2 ለ 1 መሪነት ተሸጋግሮ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባጅፋሮች የቀኝ ተከላካዩ ያሬድ ዘውድነህን አስወጥተው ግብ ለማስቆጠር ያለመ በሚመስል ቅያሪ ቢስማርክ አፒያን ተክተው አስገብተው በሁለት አጥቂዎች የጎንዮሽ ጥምረት ለማጥቃት ሙከረመ ቢያደርጉም እምብዛም ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ሀዋሳዎች በአንፃሩ በርካታ የግብ እድሎች ቢፈጥሩም በቀላሉ ሲያመክኗቸው እና በግብ ጠባቂው አጄይ ጥረት ሲከሽፉ ተስተውለዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ድልቢ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ዳንኤል አጀይ እንደምንም ያወጣት ጠንካራ ኳስ ልትጠቀስ የምትችል መከራ ናት። 

ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ 74ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ከሀዋሳ የሜዳ አጋማሸ በረጅሙ የላካትን ኳስ እስራኤል እሸቱ ከተቆጣጠራት በኃላ ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ አስደናቂ ግብን አስቆጥሮ የሀዋሳ የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። ሀዋሳዎች ከጎሉ በኋላም በፍቅረየሱስ፣ እስራኤል እና ገብረመስቀል በመጨረሻወቹ ደቂቃዎች ላይ የግብ ማግባት አጋጣሚን መፍጠር ሲችሉ ጅማ አባጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጓት አንድ ሙከራ ብቻ ነበረች። መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ላይ ኄኖክ ገምቴሳ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ቢስማርክ አፒያ በግንባር ገጭቶ ሶሆሆ የያዘበት ሙከራ ብቸኛው ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር። 

ጨዋታው በሀዋሳ 3-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳዎች የደረጃ ለውጥ ባያደርጉም ነጥባቸውን 17 በማድረስ ከመሪው ቡና ያላቸውን ነጥብ ሲያጠቡ ምንም እንኳን ሶስት ተስተካካይ ጨዋታ ቢኖረውም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል ማግኘት ያልቻለው ጅማ አባ ጅፋር በ6 ነጥቦች 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *