የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 3-1 ጅማ አባጅፋር 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባጅፋርን 3-1 ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

“ማሸነፋችን ጥሩ ነው፤ አሁንም ግን የሚቀረን ነገር አለ” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” ማሸነፋችን ጥሩ ነው፤ አሁንም ግን የሚቀረን ነገር አለ። ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ስንገባ በቁጥር በዝተን በጥሩ ሁኔታ ነው። ጎል ላይ ያለንን ስልነት ግን አሁንም ቢሆን ማስተካከል አለብን። ይህን ለማድረግ ደግሞ ስራ ይጠይቀናል። የዚህ ምክንያቱ ጉጉት ነው፤ ወይም አካሄዳችን ነው። ከኋላ ተነስተን ፈጥነን ወደ አደጋ ክልል ስለምንገባ ግብ ጋር ስንደርስ የምንወስነው ውሳኔ ላይ ችግር አለብን። ”

ስለ አጨራረስ ድክመት

” አሁንም እየታየ ያለው የኛ ግብ ጋር መድረስ ነው። ባንደርስ ደግሞ እነዚህ ስህተቶች አይታዩም ነበር። በእርግጥ የምናመክናቸው ኳሶች ለተመልካችም ለኛም ያጓጓሉ።

” ዛሬ የመጀመሪያ አይደለም፤ ከሽረም ጋር ስንጫወት እንደዚህ ግብ ገብቶብን ስድስት ጎል ነው ያገባነው። ዛሬም ገብቶብን ሶስት ግብ ነው ያገባነው። እንደሌላው ቡድን ይህን ስናይ ከበቂም በላይ ነው ትላለህ። ዛሬ ቡድኖች ላይ የሚገባው አንድ ጎል፣ ሁለት ጎል፣ ባዶ ለባዶ… ከዚህ ውጭ ሌላ ጎል አይታይም። እኛ ጋር ግን በርካታ ጎሎች ይቆጠራሉ። ቢሆንም የምንሄደው አካሄድ የበለጠ ማግባት የምንችልበት ነው። ይህ ደግሞ አንድ ነገር ያሳየናል፤ ተጫዋቾቻችን በሙሉ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ሳጥን ውስጥ ጠብቆ የሚያስቆጥር ተጫዋች የለንም፡፡

” አቅም ጨርሰናል ” ዩሱፍ ዓሊ – የጅማ አባጅፋር ረዳት አሰልጣኝ

ስለ ጨዋታው

“በዛሬው ጨዋታ እንደተመለከታችሁት አቅም ጨርሰናል። አቅም አላቸው፣ ለዚህ ሜዳ ይሆናሉ ያልናቸው ተጫዋቾች ተጎድተውብናል። ዛሬ እነ መስዑድንም ማየት ይቻላል፤ እሱ ከተጎዳ በኋላ ጥሩ አልነበርንም። ከጨዋታ ያወጣን ግን ዳኛው ነው፤ ቀድመን ጎል ብናስቆጥርም ከፍፁም ቅጣት ምቱ በኋላ ተጫዋቾቹ እየወረዱ መጡ። በአጠቃላይ ግን የአቅም ጉዳይ ነው። በየሶስት ቀኑ እየተጫወትን ከመሆኑ በተጨማሪ ሁለቴ በዚህ ሜዳ ተጫውተናል። ይህ ደግሞ አቅም ይጨርሳል። በተደጋጋሚ ልምምድ ካልሰራህበት አቅም ያሳጣሀል። ይህ ነገር ደግሞ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል።”

ስለተወሰደባቸው ብልጫ እና የእረፍት ሰዓት ቅያሪ

“ዲዲዬ ለብሬን እንዳየኸው ከሆነ ይከላከላልም ያጠቃልም። እንዲህ አይነት ባህሪ ስላለበት አብዛኛውን ደግሞ ቡድንህ ሲመራ የማጥቃት ባህሪ ያለውን ሰው ነው የምታስገባው። ዲዲዬ ወደ መከላከሉ መልሰን የሚከላከል ተጫዋች አስወጥተን ቢስማርክ አፒያን አስገብተናል። የመጀመሪያ አስር ደቂቃ ጥሩ ነበርን ቢሆንም ተጋጣሚያችንን ያነሳሳው ፍፁም ቅጣት ምቱ ነው አግባብ ያልሆነም ነበር የተሰጠብን ውሳኔ። ይህ ደግሞ እኛ እንድንወርድ አደረገን። በአጠቃላይ ግን አቅም በመጨረሳችን ነው ብልጫ የተወሰደብን።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *