የድሬዳዋው አጥቂ የስምንት ጨዋታዎች እገዳ ተላለፈበት

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ እና ስምንተኛ ሳምንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ላይ በተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈቶች ዙርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አስተላልፏል። 

ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ድረዳዋ ከተማ 1-1 በተለያዩበት የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ ፍፃሜ ላይ የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ኢታሙኑዋ ኬይሙኔ የድቻው ሙባረክ ሰየሽኩሪን በቦክስ በመማታቱ እና በስፍራው የነበረውን ተመልካች ለአፀፋ ጥቃት በማነሳሳቱ የ8 ጨዋታዎች እገዳ እና 15 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል። ናሚቢያዊው አጥቂ እስካሁን በሊጉ ለድሬዳዋ አራት ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ቢያንስ ለቀጣዮቹ ሁለት ወራት በእገዳው ምክንያት ብርቱካናማ ለባሾቹን አያገለግልም።

በዚሁ ጨዋታ ማብቂያ ላይ ከ500-700 የሚገመቱ የወላይቻ ድቻ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው በመግባት የድሬዳዋ ተጫዋቾች እና አመራሮች ላይ ዛቻ መሰንዘራቸውን የገለፀው ፌዴሬሽኑ የድሬዳዋ መኪና እና ሾፌር በደረሰባቸው ጥቃት የወደመውን ንብረት ወጪ እና የሾፌሩን የህክምና ወጪ ወላይታ ድቻ እንዲሸፍን ተወስኗል። 

በስድስተኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የተከሰተውን የደጋፊዎች ግጭት በተመለከተ የሊግ ኮሚቴ በቀጣዩ ቀን በዝግ ስታድየም እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፎ ጨዋታውም በመደረጉ ተጨማሪ ውሳኔ እንዳልተላለፈ የዲሲፕሊን ኮሚቴው አስታውቋል። 

Leave a Reply