ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | ጅማ አባ ጅፋር ለነገው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ዛሬ ሰርቷል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በአል አህሊ ተሸንፎ ከአንደኛው ዙር የወደቀው ጅማ አባ ጅፋር ወደ ኮፌዴሬሽን ካፕ ምድብ ድልድል ለመግባት ነገ 10:00 በአዲስ አበባ ስቴዲየም ከሞሮኮው ሀሳኒያ ዩኤስ አጋዲር ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ከማድረጉ አስቀድሞ ዛሬ የመጨረሻውን ልምምዱን ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስቴዲየም አከናውኗል።

በተደራራቢ ጨዋታ በጉዳት በርከት ያሉ ተጫዋቾቹ እንደተጎዱበት እየተገለፀ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከነገው የኮፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ አስቀድሞ ባልተሟላ ሁኔታ የመጨረሻ ልምምዱን ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስቴዲየም አድርጓል። በንድፈ ሀሳብ እና በሜዳ ላይ ባተኮረው የዛሬው ልምምድ 18 ተጫዋቾች ብቻ የተገኙ ሲሆን ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ፣ ዐወት ገብረሚካኤል፣ ኤልያስ አታሮ እና ሄኖክ ገምቴሳ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ መስዑድ መሐመድ ከጉዳቱ አገግሞ ለነገው ጨዋታ መድረሱ ለቡድኑ መልካም ዜና ሆኗል ።

ለአንድ ሰአት በሜዳ ላይ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ከሰራ በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ትንሿ አዳራሽ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለአርባ አምስት ደቂቃ የፈጀ በፕሮጀክተር የተደገፈ የታክቲክ እና የስነ ልቦና ትምህርቶችን ወስደዋል።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ተደጋጋሚ ጨዋታ ማድረጋቸው በቡድኑ ላይ ጫና እና ጉዳት ያስቸገራቸው እንደሆነ ገልፀው ባሉት ተጫዋቾች የሚቻለውን ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የሞሮኮው አጋዲር ከሰሜን አፍሪካ ቡድኖች የተለየ አጨዋወት እንደማይኖረው የገለፁት አሰልጣኙ “ከአል አህሊ ጋር ያደረግነው የደርሶ መልስ ጨዋታ ብዙ ነገሮችን ተምረንበታል። ለነገ ጨዋታ ውጤቱን ይዘን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።” ብለዋል።

ከ30 በላይ የሉዑክ ቡድን በመያዝ ሐሙስ አዲስ አበባ የገባው ዩኤስ ሀሳኒያ አጋዲር ትላንት በአዲስ አበባ ስታዲየም የመጀመርያ ልምምዱን የሰራ ሲሆን ዛሬ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከመከላከያ ጨዋታ በማስከተል የመጨረሻ ልምምዱን የሚያከናውን ይሆናል።

ነገ በ10:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄደውን ጨዋታ የሚመሩት ማሊያዊያኑ ቦውቡ ትራኦሬ (ዋና)፣ ባባ ዮምቦሊባ (1ኛ ረዳት)፣ ካሞሪ ኒያሬ (2ኛ ረዳት) እና ሴይቡ ካኔ (4ኛ) ሲሆኑ ኬንያዊው ሲልቬስተር ክሪዋ በኮሚሽነርነት ተመድበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *