የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-1 መቐለ 70 እንደርታ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ በተደረገው ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ባለሜዳውን ሀዋሳ ከተማን ማሸነፍ ችሏል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

” መቼ ማጥቃት እንዳለብን አስበን ነው የገባነው ” ገብረመድህን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ

” እንደሚታወቀው ሀዋሳዎች በሜዳቸው ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት አቅም አላቸው። ሜዳውን በደንብ ያቁታል እኛ ደግሞ ታክቲካሊ መቼ ማጥቃት እንዳለብን አስበን ነው የገባነው። የኳስ ብልጫ የሚወስዱት የሀዋሳ ቁልፍ ተጫዋቾች እነማናቸው በሚል ትኩረት አድርገን እንቅስቃሴውን ለመግታት ጥረት አድርገናል ፤እኚህን ማጥፋት ነበር ሀሳባችን። ይህን ደግሞ እያደረግን በመልሶ ማጥቃት ለማግባት ነው ያሰብነው። ተሳክቶልናል ደስ የሚል ሰላማዊ ጨዋታም ነበር፡፡ ”

የቡድኑ እንቅስቃሴ አማኑኤል እና ያሬድ ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ

“እንደውም አማኑኤል እስከ አሁን ሁለት ግብ ነው ያገባው ፤ ማግባት የሚገባውን ያህል አላገባም። በአመዛኙ እኛ ስንጫወት በጋራ የማጥቃት ነው፡፡ አንድ አጥቂ ደግሞ ግብ ማግባት ግዴታው ነው። ሁለቱ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆንም አያስፈልግም። ግን እንደቡድን ተንቀሳቅሰን ማስቆጠር ይገባናል። እንደውም እስከአሁን የአማካይ ተጫዋቾች ናቸው ግብ የሚያገቡት እና በጋራ የመጫወት አቅማችንን እናዳብራለን፡፡ ነገር ግን እነሱ ላይ ጥገኛ አይደለንም እንደ አጥቂ ግን ግብ ማግባት አለባቸው፡፡”

“ያገኘኸውን ዕድል የማትጠቀም ከሆነ ውጤቱ እንደዚህ ነው፡፡” አዲሴ ካሳ ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“እነሱ ጥሩ ናቸው ፤ እኛም ጥሩ ነበርን። ሁልጊዜ ኳስ ጨዋታ ላይ ያገኘኸውን ዕድል የማትጠቀም ከሆነ ውጤቱ እንደዚህ ነው የሚሆነው ፤ ዛሬም የሆነው ይህ ነው፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን ኳሶች እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ያገኘናቸው የመጨረሻ ኳሶች ብንጠቀም ይህ ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ ቢሆንም ግን እነሱም ጥሩ ነበሩ። እኛ በይበልጥ ትኩረታችን ማጥቃቱ ላይ እና ማሸነፉ ላይ ሆነና መሀሉን እንዲሁም መጨረሻውን መከላከሉ ላይ ተዘናጋን ፤ በዚህ አጋጣሚ የነሱም አመጣጥ ደግሞ የተሻለ ነበር፡፡”

የደስታ ቅያሪ ስለፈጠረው ክፍተት

“ትክክል ነው፡፡ መጀመሪያም መጨረሻም ላይም የታየብን ነገር ይህ ነው። በተለይ ተጫዋቾችን ከቀየርን በኃላ በይበልጥ ክፍተቱ የጎላው በዛ ቦታ ነበር። በቦታው ሲያጠቃ የነበረው የነሱ ተጫዋች አማኑኤል የተሻለም ነበር። በጣም ፈጣን ነው ፤ ኳሱን በፍጥነት ይነዳል አልፎንም ይሄዳል። ስለዚህ እሱን ማቆም አልተቻለንም። በሶስት ተከላካይ ነበር የምንጫወተው እሱ ደግሞ ከብዶን ነበር። ያስገባነውም ተጫዋች በይበልጥ የማጥቃት ባህሪ ያለው በመሆኑ የመከላከሉ ላይ ብዙም አልነበረም። የደስታ ክፍተት የተፈጠረው እኛ እናሸንፋለን የሚል ዕምነት በውስጣችን ስለነበር ነው። ያተኮርነው ግብ ማገባቱ ላይ ነው። ስለዚህ ቀይረን ያስገባናቸው ተጫዋቾች ማጥቃቱ ላይ የሚያዘነብሉ መሆናቸውን እነሱ ተጠቅመውበታል። መከላከሉ ላይ ጠንካራ ስለነበሩም ልንሰብራቸው አልቻልንም። ኳሱን ሲያገኙት ደግሞ በጣም ፈጣኖች ነበሩ። ሲወጡ እኛ ደግሞ ለመመለስ ክፍተት ነበረብን ይህ ነገር በደንብ ልዩነቱን አሳይቶናል፡፡”

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *