ኦኪኪ አፎላቢ በድጋሚ ጅማ አባ ጅፋርን ተቀላቀለ

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢ በመሆን ያጠናቀቀው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ቀድሞ ክለቡ ተመልሶ ለመጫወት ከስምምነት መድረሱ ታውቋል፡፡

የናይጄሪያ ዜግነት ያለው የፊት አጥቂው ኦኪኪ አፎላቢ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ጅማ አባ ጅፋር ባደገበት ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን እንዲያነሳ 23 ግቦች በማስቆጠር በግንባር ቀደምትነት የሚነሳ ሲሆን በክረምቱ ግን ጅማን ለቆ ወደ ግብፅ ማምራቱ ይታወሳል። በግብፅ ለኢስማኤሊ ለመጫወት ከስምምነት ደርሶም ፊርማውን አኑሮ ነበር። ሆኖም በርካታ ውዝግቦችን ያስነሳው የተጫዋቹ የዝውውር ሂደት ህጉን የተከተለ አይደለም በሚል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ቅጣት መተላለፉ የሚታወስ ነው።

ለኢስማኤሊ ብዙም ግልጋሎት ሳይሰጥ የከረመው አጥቂው አሁን ወደ ጅማ አባ ጅፋር በድጋሚ የተመለሰ ሲሆን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ እስካዳር ዳምጠው ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከተጫዋቹ ጋር ጠንከር ያሉ ድርድሮች ከተደረጉ በኃላ ሊመለስ እንደቻለ ገልጸው ከፊፋ የሚጠብቁት የዝውውር ፍቃድ ከተላከላቸው በኃላ ከክለቡ ጋር ወደ ልምምድ ይገባልም ብለዋል። አክለውም ቡድኑ የአጥቂ ችግር ስላለበትንም ጭምር እንደ አንድ መፍትሄ አስበው እንዳመጡትም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በአንድ ዓመት የውል ስምምነት በድጋሚ አባ ጅፋርን የተቀላቀለው አፎላቢ ከአዳማ ሲሶኮ ፣ ቢስማርክ አፒያ ፣ ማማዱ ሲዲቤ ፣ ዳንኤል አጀይ እና ዲዲዬ ለብሬ በመቀጠል ስድስተኛ የውጪ ዜግነት ያለው ተጫዋች በመሆኑ አንድ የማጥቃት ባህሪ ያለውን የውጪ ተጨዋች ከክለቡ ሊቀነስ እንደሚችል ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *