ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ | ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ተሸንፎ ወደ ምድብ ድልድል የመግባት እድሉን አጥብቧል

በቶታል ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሞሮኮው ሀሳኒያ አጋዲርን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 1-0 ተሸንፎ ወደ ምድብ ድልድል የመግባት እድሉን አጥብቧል።

የቡድኑን የተወሰኑ ተጫዋቾችን በጉዳት እና በቅጣት ያጣው ጅማ አባ ጅፋር በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገባ በተመሳሳይ የሞሮኮው ዩኤስ ሀሳኒያ አጋዲርም ወሳኝ ተጫዋቾችን በጉዳት ይዞ እንዳልመጣ በተነገረበት በዚህ ጨዋታ ላይ 4-4-2 አደራደርን በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል። 

አባጅፋሮች በጨዋታው ጅማሬ ላይ በፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ጎል ለመድረስ እና ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት በጎል ሙከራ የታጀበው ገና በ3ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ዲዲዬ ለብሪ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል ሁኔታ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫውን ቀይሮ አንጋፋው ግብጠባቂ አብዱራህማን ሆሳሊን በማለፍ ገባ ሲባል የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። 

ጅማዎች አጀማመራቸው የተነቃቃ ቢመስልም በአጫጭር ቅብብል ኳሱን ተቆጣጥረው የጎል እድል ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት አቋርጠው ከተከላካዮች የሚላኩ ረጃጅሙ ኳሶች ለመጠቀም ያሰቡት አጨዋወት ኳሶቹ መድረሻቸው ሳይታወቅ ይባክኑ ነበር። ይህ አጨዋወትም አጋዲር ተጫዋቾች በመመቸት በሁለት አይነት የጨዋታ እንቅስቃሴ (በረጃጅም ኳሶች በፍጥነት ወደ ጎል በመድረስ እና ከማዕዘን ምትና የቆሙ ኳሶች በሚገኙ የጎል አጋጣሚዎች) አደጋ ሲፈጥሩ ተስተውለዋል።  በ7ኛው ደቂቃ የቡድኑ ግዙፉ ተከላካይ እና አንበል ያሲን ራሚ በግንባሩ በመግጨት ጠንካራ ሙከራ አድርጎ ዳንኤል አጄ ያዳነበትም እንደ ማሳያ የሚጠቀስ ነበር።

አባጅፋሮች ወደ ረጃጅም ኳሶች ከተቀየረ በኋላ በአጋርዲ ብልጫ እንዲወሰድባቸው ያደረጋቸው ሲሆን በ29ኛው ደቂቃ ሰርቢያዊው የመስመር አጥቂ በመልሶ ማጥቃት በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ነፃ አቋቋም ላለው አጥቂው ባድር ካቻኒ ሊያቀብለው ሲል የጅማው ግብጠባቂ ዳንኤል አጄ ከግብ ክልልሉ በመውጣት ኳሱን የተቆጣጠረበት፣ አጥቂው ባዳር ካቻኒ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ያገኘውን የጎል አጋጣሚ ዳንኤል አጄይ እንደምንም ያዳነበት ጎል መሆን የሚችሉ እድሎች ነበሩ። 


አጋዲር የራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በብዛት ሆነው በመጫወታቸው ጅማ አባጅፋር ይህንን አስከፍተው ለማለፍ የተቸገሩ ሲሆን ዲዲዬ ለብሪ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ የተሻለ እንቅስቃሴ ሳንመለከት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ የተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል የተመለከትን ሲሆን በተለይ በጅማ አባጅፋሮች አስቻለው ግርማ ከማዕዘን ምት የሚያሻግራቸው ኳሶች በተከላካዮች ተደርበው ሲመለሱ በሁለት አጋጣሚዎች ኤልያስ ማሞ እና ማማዱ ሲዲቤ የፈጠሩት ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ። 


ጅማዎች የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተዳከሙ ሲመጡ አጋዲሮች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች በመልሶ ማጥቃት የሚፈጥሩት አደጋ ተጠናክሮ ቀጥሎ በ62ኛው ደቂቃ አማካዩ ኤልማሀዲ ኦቢላ ከቀይ መስመር ያሻገረለትን ተቀይሮ የገባው አብዱላሊ ካንቦውቢ ደገፍ አድርጎ ወደ ጎል የመታውን ዳንኤል አጄይ ያዳነበት፣ 70ኛው በመልሶ ማጥቃት ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ ለጅማ አባጅፋር ተከላካዮች ፈተና የነበረው አጥቂው ባድር ካቻኒ ከመሐል ሜዳ ወደፊት ተከላካዮችን አልፎ በመሄድ ከሳጥን ውጭ ለአብዱላሊ ካንቦውቢ አቀብሎት አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄዮ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ አጋዲሮች የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ስመሆኑን ማሳያ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ እንደወሰዱት ብልጫ 74ኛው ደቂቃ ዞሒር ቻውች እጅግ አስገራሚ የሆነ ጎል ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል። ለጎሏም በስታዲየሙ የነበረውን ተመልካች አድናቆቱን ችሮታል።  


አጋዲሮች ከጎሉ በኀላም በመልሶ ማጥቃት በተመሳሳይ ሌሎች የጎል አጋጣሚ ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። የአቻነት ጎል ፍለጋ አባጅፋሮች በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞክሩም 90ኛው ደቂቃ መስዑድ መሐመድ እና ኤልያስ ማሞ በአንድ ሁለት ቅብብል ለሲዲቤ አቀብለውት በግቡ አናት ለጥቂት ከወጣበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በእንግዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ አጋዲር ላይ በቀጣዩ ሳምንት ሲደረግ ጅማ ወደ ምድብ ድልድል ለመግባት ከአንድ ጎል በላይ አስቆጥሮ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *