ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ወልዋሎ ዓ/ዩ አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት በተቃውሞ በታጀበው ጨዋታ  ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ  ከወልዋሎ ጋር ተገናኝቶ ነጥብ ተጋርቷል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ በነበሩበት 30 ደቂቃዎች የወላይታ ስታድየም ከሚታወቅበት ድባቡ የተቀዛቀዘ ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት በስታድየሙ የነበረው እና እስከ ጨዋታው መጠናቀቅ ድረስ በአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ላይ ከተሰማው ከፍተኛ ተቃውሞ ጋር የሚያያዝ ነው።

ወላይታ ድቻ በደደቢት ከተረታበት ጨዋታ ቀዳሚ ተሰላፊዎች ውስጥ  ሙባረክ ሽኩር ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ ፍፁም ተፈሪ እና ፀጋዬ አበራን በማስወጣት  በምትካቸው ኄኖክ አርፊጮ ፣ እዮብ ዓለማየሁ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና ሳምሶን ቆልቻ ተክቶ ገብቷል። በኢትዮጵያ ዋንጫ በፋሲል ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው ወልዋሎዎችም በረከት አማረ ፣ በረከት ተሰማ ፣ ሮቤል አስራት ፣ ሳምሶን ተካ ፣ ተስፋየሰ ዲባባ ፣ ዳዊት ፍቃዱ ፣ አብዱልራህማን ፉሴይኒን አስወጥተው  በምትካቸው አብዱልዓዚዝ ኬይታ ፣ ቢንያም ሲራጅ ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ብርሃኑ ቦጋለ ፣ አፈወርቅ ሃይሉ ፣ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ሬችሞንድ አዶንጎን ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ተካተዋል።

ፌዴራል ዳኛ ወልዴ ንዳው ጨዋታውን በብቃት ከመመራቱ ውጪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው እጅጉን አሰልቺ እና ሙራዎችን ከማድረግ እና የግብ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ይልቅ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ሆኖ ሲታይ ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ወደ ማጥቃት ወረዳው ለመግባት ይልተሳኩ ጥረቶች ያደረጉበትም ነበር። ወልዋሎዎች በግራ መስመር ከተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለ ከሚሻገሩ ኳሶች እና ወደ ኤፍሬም አሻሞ የቀኝ መስመር አመዝነው ለማጥቃት ሲሞክሩ ወላይታ ድቻዎች በተደጋጋሚ በሚባክኑ ረጃጅም ኳሶች በግራ ተከላካዩ ሄኖክ አርፊጮ አማካኝነት ወደ አንዱዓለም ንጉሴ እና ባዬ ገዛኸኝ በመድረስ ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራን ያደረጉ ቢሆንም ውጤታማ ሲሆኑ ግን መመልከት አልቻልንም፡፡


ወላይታ ድቻዎች በኄኖክ በኩል በሚገኙ ዕድሎች ግብ ለማግኘት በሚያደርጉትን ጥረት በይበልጥ ቢጠቀሙም አንዱዓለም እና አጋጣር ሲደርሱ በቀላሉ ይባክናሉ፡፡  ኄኖክ ሁለት ጊዜ አሻግሮ ሁለቱም አጥቂዎች በቀላሉ ያገኙትን አጋጣሚ መጠቀም ያልቻሉበት እና እዮብ አለማየሁ ወደ ሳጥን ጠርዝ ተጠግቶ ለአንዱዓለም  የላከለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ አብዱላዚዝ ኬይታ የያዘበት በድቻ በኩል ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ። በ36ኛው ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ላይ በተሰራ ጥፋት በሳጥኑ ጠርዝ  የተገኘችውን የቅጣት ምት ኄኖክ መትቶ በግብ ጠባቂው ኬይታ እንደምንም ልትወጣ ችላለች። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንዱዓለም በረጅሙ ለቸርነት ጉግሳ ሰጥቶት ቸርነት በቀላሉ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ወደ ኤፍሬም አሻሞ አድልተው ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረስን ያሰቡት ወልዋሎዎች በጥልቀት ወደ ውስጥ ገብተው በሪችሞንድ እና ፕሪንስ በኩል ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ጥቃት ግን ውጤታማ ሲሆን አልተስተዋለም፡፡ ሪችሞንድ በተደጋጋሚ ሲደርሱት የነበሩትን ግለፅ ዕድሎች ከማምከን ውጪ ወደ ግብነት ለመቀየር ሲቸገርም ነበር፡፡ ኤፍሬም አሻሞ የድቻን የተከላካይ ክፍል ሰብሮ ለመግባት በግሉ ጥረት ቢያደርግም በጥብቅ ሲከላከሉ የነበሩት ድቻዎች በተደጋጋሚ ሲያስጥሉት አስተውለናል፡፡ በወልዋሎ በኩል ልትጠቀስ የምትችለው 24ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ኃይሉ ከርቀት አክርሮ መትቶ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት ሙከራ ነች። ነገር ግን ሁለቱም ቡድኖች ከሚያደርጉት አሰልቺ እንቅስቃሴ ውጪ ጠንካራ የግብ ማግባት አጋጣሚን ሳንመለከት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡


ከዕረፍት መልስም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የተለየ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን በሁለቱም ቡድኖች ብበከል መመልከት አልተቻለም። ድቻዎች ጫን ብሎ ግብ ለማስቆጠር በተሻለ መንቀንቀሳቀስ ቢችሉም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ ሲባክን እንጂ የተጋጣሚውን የግብ በር ለመፈተሽ የሚያስችል ሆኖ አልታየም፡፡   ወልዋሎዎች ትኩረት አድርገውት የገቡት የኤፍሬምን የቀኝ መስመር በሚገባ ለመጠቀም እንጂ ከሱ ውጪ ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ውጤታማነቱ እምብዛም ነበር። 46ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሪችሞንድ እና ፕሪንስ ያገኙት ዕድል ለአማኑኤል ጎበና ሰጥተውት አማኑኤል መትቶ የወጣበት ወልዋሎዎች  ያደረጉት ቀዳሚ ሙከራ ነበር፡፡

ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በእዮብ ዓለማየሁ እና ቸርነት ጉግሳ አማካኝነት ሁለት ጊዜ ለግብ መቅረብ ቢችሉም ኬይታ በቀላሉ ይዞባቸዋል። በመቀጠል 63ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ሲራጅ በራሱ የግብ ክልል ጠርዝ በግራ በኩል ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ድቻን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ወደ ፊት በሚላኩ ኳሶች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የተቃረቡት ድቻዎች 81ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከግቡ ትይዩ ተገናኝቶ ኬይታ በአስገራሚ ሁኔታ ያወጣበት መከራቸው ተጠቃሽ ነበር፡፡

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግን ወልዋሎዎች አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሶስት ደቂቃ ሲቀረው 87ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል ተነስተው በመልሶ ማጥቃት መጫወት የቻሉት ወልዋሎዎች ኳስ ኤፍሬም አሻሞ ጋር ደርሳ ወደ ውስጥ ፈጥኖ ለገባው እንየው ካሳሁን አሳልፎለት እንየው ወደ ግብነት ለውጧት ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቅ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን ተጫዋቾችም በዚህ የተነሳ ከ30 ደቂቃ በላይ በሜዳ ላይ ለመቆየት ተገደዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *