ከፍተኛ ሊግ ለ | ወልቂጤ በአሸናፊነት ጉዞው ቀጥሏል

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለሰባተኛ ሳምንት ሁሉም ጨዋታዎች እሁድ ተከናውነው ወልቂጤ ከተማ በአሸናፊነቱ ሲቀጥል ሀምበሪቾ፣ ሀላባ ከተማ እና ኢኮስኮ ከሜዳቸው ውጪ ተጋጣሚያዎቻቸውን አሸንፈዋል። 

ከዕለቱ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ በ4:00 ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ሀምበሪቾ ያደረጉት ጨዋታ በእንግዳው ቡድን 3-0 አሸናፊነት ተደምድሟል። የመጀመሪያውን የጨዋታ ክፍለ ግዜ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ ከእረፍት መልስ ተጠናክሮ የገባው ሀምበሪቾ ፋሲል ባቱ በ48ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁም አብነት ተሾመ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ማድረግ ችሏል። 

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን በኢኮስኮ ሽንፈት ገጥሞታል። ለኢኮስኮ ወደ ድል የተመለሰባትን ብቸኛ ጎል ማስቆጠር የቻለው የኋለሸት ሰለሞን ነው። በውጤቱ ኢኮስኮ ደረጃውን ወደ ሦስተኛ ከፍ ሲያደርግ መድን ከሁለተኛ ወደ አራተኛ ዝቅ ብሏል። 

ወልቂጤ ላይ ወልቂጤ ከተማ ከዲላ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በባለሜዳው ወልቂጤ የተመስገን ደረሰ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ባለፈው ሳምንት ከሜዳው ውጪ 7-1 አሸንፎ የተመለሰው ወልቂጤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የምድቡን መሪነት ማጠናከር ችሏል።

አዲስ አበባ ከ ወላይታ ሶዶ 1-1 አቻ ተለያይተዋል። ኢብሳ በፍቃዱ የአዲስ አበባን ጎል ሲያስቆጥር ሲሳይ ማሞ የሶዶን ጎል ማስቆጠር የቻለ ተጫዋች ነው።

የዛሬ ሳምንት በወልቂጤ አስከፊ የ7-1 ሽንፈት የገጠመው ናሽናል ሴሜንት ወደ ነገሌ አርሲ ተጉዞ ነገሌ አርሲን 1-0 በማሸነፍ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክ/ከተማን የገጠመው ሀላባ ከተማ 2-0 አሸንፎ ተመልሷል። የበርበሬዎቹን የድል ጎሎች ማስቆጠር የቻሉት ምትኩ መሜጫ እና ብዙዓየሁ ሰይፉ ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *