ከፍተኛ ተቃውሞ ያስተናገዱት አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ከወላይታ ድቻ ጋር ሊለያዩ ይሆን ?

ወላይታ ድቻን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት አጋማሽ የተረከቡት አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ከደጋፊዎቹ ዘንድ እየተነሳ ባለው ጠንካራ ተቃውሞ ምክንያት ከወላይታ ድቻ ጋር የመቀጠላቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

በ2010 አጋማሽ መሳይ ተፈሪን በመተካት በጊዜያዊነት አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት ዘነበ ፍስሀ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ቋሚ ውል ከፈረሙ በኋላ ቡድኑን በአዲስ መልኩ በማወቀር አስር ሳምንታትን የተሻገሩ ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን በደጋፊው ተቃውሞ እየተሰማባቸው ይገኛል። ትላንት በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን በ10ኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ገጥሞ 1-1 ከተለያየበት ጨዋታ አስቀድሞ ባሉት ሰላሳ ደቂቃዎች አንስቶ እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ድረስ በስታዲየሙ የተገኙት የክለቡ ደጋፊዎች የአሰልጣኙን ስም በመጥራት፣ በክለቡ ያሉ አመራሮች እና ተጫዋቾችን ጭምር በመጥቀስ ሲቃወሙ አስተውለናል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ የተቃውሞን ምክንያት ለማጣራት ባደረገችሁ ጥረት አሰልጣኙ እያስመዘገበው ባለው ውጤት ደስተኛ አይደለንም የሚል ሲሆን ከአሰልጣኙም ጋር በግል ቅራኔ ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ሆን ብለው ያደረራጁት ነው የሚሉ መረጃዎችንም አግኝተናል፡፡

የትላንቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተቃውሞው ጠንከር በማለቱ የክለቡ ተጫዋቾች በስታዲየሙ ከ30 ያህል በላይ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደዋል። የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀም ስለ ሁኔታው ጠይቀናቸው እንዲህ ብለዋል፡፡ “ዛሬ ያየሁት ነገር ለኔ አበሳጭቶኛል። በግልም እየተጠራን ስንሰደብ ነበር። በተቻለ መጠን ውጤት አስጠብቆ ለመውጣት ጥረት አድርገናል። ተጫዋቾቼ ጥሩ ተጋድሎን አድርገዋል። ደግሞም ቡድኑ ያለበት ደረጃ ሰዉን ለዚህ የሚያነሳሳ አይደለም። ከሌሎቹ ቡድኖች የተሻለ ነጥብ ስላለን ለወራጅነት የሚጫወት ቡድን አይደለንም። የሚያሳደብ እና ለተቃውሞ የሚሆን ምክንያት እንኳን የለም። በዚህ ላይ ተጫዋቾቼ እየተሰደቡ ሜዳ ውስጥ በእልህ የሚያደርጉትን አያውቁም ነበር። ” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ ከሁኔታው በኋላ በስራቸው ለመቀጠል እንደሚቸገሩም በዚህ መልኩ ገልፀው ነበር። “እኔ ከቡድኑ ጋር ባልቀጥል ደስ ይለኛል። በራሴ ወስኛለው፤ በእኔ ቦታ ሌላ ሰው ይፈልጉ። ምክንያቱም በእንደዚህ አይነት ተቃውሞ እንኳን እኔ ተጫዋቾቼ ለመጫወት ይቸገራሉ። ምናልባት እኔ ከሆንኩ የዚህ ቡድን ችግር ፈጣሪ አዲስ አሰልጣኝ ከተቀየረ በነፃነት ሊጫወቱ ይችላሉ። እኔ ፈጣሪ ወይም ክርስቶስ አደለሁም፤ በአንድ ጊዜ መና አላወርድም። በሂደት ግን እግርኳስ ስለሆነ ብዙ ነገር ይሰራል። ገና ከጅምሬ በአራት ወር ውስጥ ተቃውሞ የምታሰማ ከሆነ ይህ ከባድ ነው። በእግር ኳስ አሸንፋለሁ ብለህ ነው የምትሄደው። ግን የሚያጋጥምህን ነገር አታውቅም። ስለዚህ የሚመጣውን ደግሞ በፀጋ ትቀበላለህ።

” አሁን እኔ ምን እንደተፈጠረ አልገባኝም። ይህ ደግሞ ቡድኑን የሚጠሉ ግለሰቦች የሚሰሩት ስራ ነው። በግል እኔን መጥላት ይችላሉ። ቡድኑን ግን ሊጠሉ አይገባም። የሚያስቡ ከሆነ ቡድኑ ለእግርኳስ ወዳዱ የወላይታ ህዝብ መኖር አለበት። እኔ ግን ከአሁን ሰአት ጀምሮ ከቡድኑ ጋር መቀጥል አልፈልግም። ባለፈውም ከደደቢት ጨዋታ በፊት ሌላ አሰልጣኝ እንዲፈልጉ ስጠይቃቸው ነበር። ከኔ በኃላ የሚመጣው አሰልጣኝ መልካም ነገር እንዲገጥመው እመኛለሁ። ” ሲሉ ነበር የገለፁት፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን የክለቡን ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶን አናግረን አሰልጣኙ በክለቡ አሰልጣኝነት የቀጠል ፍላጎት እንደሌላቸው ስለመግለፃቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል። ” እኛ እስከምናውቀው ተቃውሞው ውጤትን መሠረት ያደረገ ነው። ይህ ተቃውሞ የጀመረው ከመከላከያ ጨዋታ ጀምሮ ነው። ይህ ደግሞ ልክ ነው ማለት አይቻልም። አሰልጣኙ በገባው ውል መሠረት እና ጊዜን ጠብቆ  ነው መስራት ያለበት። የይልቀቅ ጥያቄ ከህዝብ ቢመጣም እንኳ ክለቡ በቦርድ ተሰብስቦ ውጤታማ ካልሆነ በህጉ መሠረት ብቻ ነው የሚስተናገደው። አሰልጣኙ እንደተናገረው እለቃለሁ ሲል ሰምተናል። የሚቻል ከሆነ አረጋግተን ወደ ስራው እንዲመለስ እንፈልጋለን። እኛ በዚህ ሰዓት ሌላ አሰልጣኝ ለመቅጠር አልተዘጋጀንም። ባለው ጊዜ ከቦርድ ጋር ተነጋግረን የምንወስን ይሆናል። የኛ ሰው ውጤት ይፈልጋል፤ ዘንድሮ በርካታ ግዢ ስለፈፀምን ህዝቡም ከዚህ የተሻለ ነገርን ይፈልጋል። ሆኖም ጊዜው ውጤት ጠፋ የሚባልበት አይደለም፤ ገና ነው፡፡ ይህን ስላልጠበቅነው ከቦርድ ጋር ተነጋግረን እንወስናለን፡፡ ” ሲሉ ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡

አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ከክለቡ በገዛ ፍቃዳቸው ለመልቀቅ የወሰኑ ቢሆንም የክለቡ የበላይ አመራሮች ዛሬ ረፋድ ከአሰልጣኙ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን አሰልጣኙ ላይ አግባብ ያልሆኑ ተቃውሞ እንዲነሳ ያደረጉትን ተጠያቂ በማድረግ  እና በማስማማት ከክለቡ ጋር እንዲቀጥሉ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ዘነበ ፍስሀም ከክለቡ ጋር በዋና አሰልጣኝት ይቀጥላሉ ተብሏል። ይሁንና ተቃውሞው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ የክለቡ ቆይታ አጠራጣሪ መሆኑ አይቀርም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *