ሴቶች 2ኛ ዲቪዝዮን | መቐለ ከመሪው ያለውን ልዩነት ሲያጠብ አቃቂ ቃሊቲ ነጥብ ጥሏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲከናወኑ መቐለ 70 እንደርታ ተከታታይ አምስተኛ ድሉን አስመዝግቧል። መሪው አቃቂ ቃሊቲ ነጥብ ሲጥል አዲስ አበባ ላይ የተደረጉ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 

መቐለ 70 እንደርታ 2-1 ሻሸመኔ ከተማ

(በማቲያስ ኃይለማርያም)

ማራኪ ጨዋታ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢታይም ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በርካታ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ዮርዳኖስ ሙዑዝ ከመስመር በጥሩ ሁኔታ ገብታ አሻምታው የሻሸመኔ ተከላካዮች ተረባርበው ባዳኑት ሙከራ የጀመሩት መቐለዎች ብዙም ሳይቆዩም በገነት ኃይሉ ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም የሻሸመኔዋ ግብ ጠባቂ ብርሃኔ ባልቻ አድናዋለች።

ቀስ በቀሰ አጨዋወታቸው ቀጥተኛ በማድረግ ወደ ብቸኛ አጥቂያቸውን መሰረት አድርገው ማጥቃት የጀመሩት ሻሸመኔዎች በአስራ ስምንተኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። እናት ያደታ ከርቀት አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግሩም ግብ ነበር ቡድኗን መሪ ማድረግ የቻለችው።

ግብ ካስተናገዱ በኃላ የተሻለ የተነቃቁት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አቻ መሆን ችለዋል። ሊዲያ ልዑል ከቅጣት ምት ያሻማችውን ኳስ ሳሮን ሠመረ በግንባሯ በመግጨት ቡድኗን አቻ ማድረግ ችላለች።
በመስመር በሚያደርጉት ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት  ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው የግብ ሙከራ ሲያደርጉ በ27ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ የሚሆኑበትን ዕድል አግኝተዋል። በጨዋታው ኮከብ ሆና የዋለችው ሳሮን ሠመረ ከሠላም ተኽላይ በግሩም ሁኔታ የተላከላትን ኳስ ተጠቅማ ግብ በማስቆጠር ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

ሻሸመኔዎችም በመጀመርያው አጋማሽ መጨረሻ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ብርቄ አማረ ከማዕዝን የተሻማውን ኳስ ተገልብጣ በመምታት ሻሸመኔዎች አቻ ሆነው ወደ ዕረፍት የሚያመሩበት ዕድል ፈጥረው ነበር።

ከዕረፍት በኃላ ተሻሽለው የቀረቡት ሻሸመኔዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያሳኩም መቅደስ ታፈሰ እና እናት ያደታ ከርቀት ካደረገችው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። በአንፃሩ በቀጥተኛ አጨዋወት ለማጥቃት የሞከሩት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም በጨዋታው ከቆሙ ኳሶች በርካታ ሙከራዎች ያደረገችው ሊዲያ ልኡል የፈጠረቻቸው የግብ እድሎች ይጠቀሳሉ።


የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ

(በዮናታን ሙሉጌታ)

09፡00 ላይ የተገናኙት ቦሌ ክ/ከ እና ቂርቆስ ክ/ከ ጨዋታቸውን ያለግብ አጠናቀዋል። በጨዋታው አብዛኛው ክፍል በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ የበላይነት ያነበራቸው ቦሌዎች በቤተልሄም ምንታሉ እና ሜሮን አበበ አማካይነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ማስቆጠር አልሆነላቸውም። ከዕረፍት መልስም በቀኝ መስመር በአንበሏ ምስጋና ግርማ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለው ነበር። በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር አቅደው የገቡ የሚመስሉት ቂርቆሶችም በሬዱ በቀለ በቀኝ መስመር በምትፈጥረው ጫና ታግዘው የግብ ዕሎችን ፈጥረዋል። ከበሬዱ በተጨማሪም ሎሚ አብሽ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ  ስታግዝ ታይታለች። ሆኖም ጨዋታው ያለግብ እንዳይጠነቀቅ የሚያደርግ ጎል ከሁለቱም ቡድኖች በኩል ሳይገኝ ከተቀዛቀዘ ሁለተኛ አጋማሽ በኋላ ፍፃሜውን አግኝቷል።


በሁለተኝነት ከ11፡00 ጀምሮ የተደረገው የልደታ ክ/ከተማ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ከአየሩም ቀዝቀዝ ማለት ጋር ተያይዞ ፈጠን ያለ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ነበር። ነገር ግን ምንም እንኳን የተወሰኑ ሙከራዎች ቢደረጉበትም የመጀመሪያ ግብ የተስተናገደበት ቡድኖቹ ወደ እረፍት ሊይመቱ ሰከንዶች ሲቀሩ ነበር። የግቧ ባለቤት የልደታ ክፍለ ከተማዋ መስታወት ግመሌ ስትሆን ከርቀት ከፍ አድርጋ የመታቻት ኳስ በንፋስ ስልኳ ግብ  ጠባቂ ዮርዳኖስ ኃይሌ አናት ላይ አልፋ ከመረብ አርፋለች። 

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ የፉክክር መጠኑ ከፍ ብሎ የቀጠለ ሲሆን ንፋስ ስልኮች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው መጫወት ቀጥለው 79ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥን ውስጥ በእጅ በተነካ ኳስ ምክንያት የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። እየሩስ ወንድሙም አጋጣሚውን ወደ ግብነት መቀየር ችላለች። በቀሩት ደቂቃዎች ልደታዎች በቤተልሄም አሰፋ እና ነፃነት ደርቤ አማካይነት ያደረጓቸው ሙከራዎች በግቡ አግዳሚ እና በንፋስ ስልክ ግብ ጠባቂዋ ዮርዳኖስ ጥረት ድነው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ጎንደር ላይ ረፋድ 4:00 የተካሄደው የፋሲል ከነማ እና አቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት አቃቂዎች ምንም እንኳን እስካሁን ሽንፈት ባያስተናግዱም መቐለ በተስተካካይ ጨዋታ ፋሲልን ካሸነፈ መሪነቱን የሚያስረክብ ይሆናል። 

የሁለተኛ ዲቪዝዮን ጨዋታዎች ዛሬ የተጠናቀቁ ሲሆን ጥር 13 መቐለ ላይ በመቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ብቸኛው ተስተካካይ መርሐ ግብር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *